“የማትበገር ሀገር ሠራዊት በመኾናችሁ ልትኮሩ ይገባል” ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ

45
ባሕር ዳር: ጥር 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ በጎጃም ቀጣና በግዳጅ ላይ ተሠማርቶ የሚገኘውን የመከላከያ ሠራዊት የሥራ እንቅስቃሴ በቦታው ተገኝተው አበረታተዋል።
የምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ እና የቀጣናው የጸጥታ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ሌተናል ጀኔራል መሐመድ ተሰማ በአዴት ዙሪያ እና በይልማና ዴንሳ ወረዳ ተዘዋውረው ሠራዊቱን ተመልክተዋል።
የሠራዊቱን እና የክልሉን የጸጥታ ኃይል የግዳጅ አፈጻጸም እና የመፈጸም አቅሙን እንዲሁም በቀጣናው ያስገኘውን ውጤት ነው የቃኙት፡፡
በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት አባቶቻችን ጠብቀው ያቆዩንን ሀገር አዲሱ ትውልድም ጠብቆ በማስቀጠል አደራን መወጣት እንደሚገባ አንስተዋል።
የውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻች እና የውስጥ ተላላኪ ባንዳዎች ሀገራችን መንግሥት አልባ አድርገው ለማፍረስ ያሰቡትን ዓላማ የማምከን ተግባራቸውን አክሽፋችኋል ብለዋል ለሠራዊታቸው። እንደ እስካሁኑ ሁሉ ወደፊትም ጠላት የገባበት በመግባት ጠንካራ ምታችሁን ማሳረፍ ይጠበቅባችኋል ነው ያሉት።
የለበስነው ሬንጀር የኢትዮጵያ ካርታ ያለበት፤ ለክብሩ ሲሉ ብዙ ጓዶቻችን መስዋዕት የከፈሉበት፤ ጠላት ከሩቁ ሲያየው የሚያስፈራ፤ “የማትበገር ሀገር ሠራዊት በመኾናችሁ ልትኮሩ ይገባል” ብለዋል።
በቀጣናው በጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራ የመጣውን ሰላም አስጠብቆ በመቀጠል በአጭር ጊዜ ግዳጃችንን መጨረስ አለብን ነው ያሉት፡፡
ጽንፈኛው አሁን ላይ በተወሰደበት የተቀናጀ ምት መግቢያ እና መውጫ አጥቶ ተደራጅቶ መዋጋት አቅቶት ተበታትኖ እና አባላቶቹም ተስፋ ቆርጠውበት እርስ በርሱ አልተማመን ብሎ አብዛኛው ኃይል የሰላምን አማራጭ ተቀብሎ እየገባ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
በአካባቢው የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት የሥራ ኀላፊ እና የዞኑ ጸጥታ ግበረ ኃይል ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄኔራል አዲሱ መሐመድ ሠራዊታችን እና የዞኑ ጸጥታ ኃይል የአካባቢው መልክዓ ምድር እና የአየር ንብረት ሳይበግረው ከክልሉ የጸጥታ ኃይል እና ኅብረተሰብ ጋር በመኾን በጽንፈኛው ላይ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት በማድረስ መቻሉን ተናግረዋል።
የይልማና ዴንሳ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ይበልጣል ሙላቴ መከላከያ ሠራዊታችን በአካባቢያችን ከመጣ ጀምሮ ኅብረተሰባችን ሰላሙን አግኝቷል ብለዋል።
እኛም ከሠራዊታችን ጎን ተሰልፈን የዚህን ዘራፊ እና ቀማኛ እየታገልን እንገኛለን ነው ያሉት። በአካባቢው ኅብረተሰቡ ተደራጅቶ ከሠራዊቱ እና ከክልሉ የጸጥታ ኃይል ጋር በመኾን ኀላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ማለታቸውን ከምሥራቅ ዕዝ ሚዲያ የተገኘ መረጃ ያሳያል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleወደ ሥራ መግባት ባልቻሉ 31 አልሚዎች ላይ እርምት ተወስዷል።
Next articleየፋይዳ መታወቂያን ለምን ከባንኮች ጋር ማስተሳሰር አስፈለገ?