የግዮን በዓልን ማክበር ፋይዳው ከክልላዊ ባሻገር ቀጣናዊ ነው።

33
ባሕር ዳር: ጥር 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ ግሽ ዓባይ ከተማ የሚገኘው የታላቁ ግዮን እና የአቡነ ዘርዓ ብሩክ ዓመታዊ ክብረ በዓል ለስምንተኛ ጊዜ በተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክዋኔዎች እየተከበረ ይገኛል፡፡
የክልሉ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ᎐ር) ለአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ እንደተናገሩት ግዮን ለኢትዮጵያ እና ለመላው አፍሪካውያን እንዲኹም ለዓለም ሕዝብ ከኩራትም በላይ የሕይዎት ምንጭ ነው፡፡
ከታላቁ የዓባይ ወንዝ መነሻ ከግዮን ታዛ ሥር በተናጠል ይከበር የነበረውን የአቡነ ዘርዓ ብሩክ ሃይማኖታዊ በዓል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ማኅበረሰቡ የግዮን እና ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱን ”የግዮን በዓል” በሚል በጋራ ሲያከብረው መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
በአማራ ክልል ትውልዱ ከሚታነጽባቸው ክብረ በዓላት አንዱ የግዮን በዓል መኾኑንም ዶክተር አየለ ተናግረዋል፡፡ ዓለምን የሚያካልለው ግዮን ለኢትዮጵያ እና ለመላው የአፍሪካውያን ሕዝቦች የመኖር ዋስትናቸው ነው ብለዋል፡፡
ያለ ግዮን ሕይዎትን ነጥሎ ማሰብ እንደማይቻል ነው ዶክተር አየለ የተናገሩት፡፡ መነሻው ኢትዮጵያ ኾኖ ካርቱምን እና ካይሮን በማካለል ሜዲትራኒያን ባሕር የሚዘልቀውን የግዮን ወንዝን በዓል ማክበር በአንድ በኩል ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ እሴትን ጠብቆ ማቆየት እንደኾነ ነው ምክትል ቢሮ ኀላፊው የተናገሩት፡፡
በሌላ በኩል የግዮን በዓልን ማክበር ትውልዱ የወንዙን ምንነት በአግባቡ አውቆ ለሃብቱ ቀናዒ በመኾን እንዲንከባከበው እና እንዲጠብቀው ያደርጋል ነው ያሉት ዶክተር አየለ፡፡
በዚህ ዓመት በዓሉ ሲከበር የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በተመረቀበት ዓመት ማግሥት መኾኑ ደግሞ ለበዓሉ ልዩ ትርጉም አለው፡፡ የግዮን በዓልን ማክበር ፋይዳው ከክልላዊ ባሻገር ቀጣናዊ ነው ያሉት ዶክተር አየለ ክልሉም ከላይ እስከ ታች ትኩረት በማድረግ በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ሰፊ ሥራ አከናውኗል፡፡
የግዮን በዓል በመከበሩ አካባቢውን በከፍተኛ ሁኔታ ማስተዋወቅ መቻሉን ጠቅሰዋል። የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን የመሳብ አቅሙም ከፍ ማለቱን ነው ምክትል ቢሮ ኀላፊው የተናገሩት፡፡
”የግዮን ልጆች ሃብታችንን እያለማን እና እየተጠቀምን ለሌሎችም በማሰብ በጋራ መኖርን መርሕ አድርገን እንቀጥላለን፤ ከዚህ ውጭ ግን የቅኝ ገዥዎችን አስተሳሰብ አንቀበልም ነው ያሉት፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያውያን የዓባይን መነሻ የመንከባከብ፣ የመጠበቅ፣ የማልማት እና የመጠቀም ኀላፊነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ዶክተር አየለ አናውጤ አሳስበዋል፡፡
የግዮን በዓል ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በክልል ደረጃ ዕውቅና ተሰጥቶት እየተከበረ እንደሚገኝም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ዘጋቢ፦ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleግሽ ዓባይ – ወላዲት ዓባይ
Next articleወደ ሥራ መግባት ባልቻሉ 31 አልሚዎች ላይ እርምት ተወስዷል።