
ባሕር ዳር: ጥር 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም ሁሉ በትልቅነቱ የሚያውቀው ስመ ጥሩው ዓባይ ወንዝ በአማራ ክልል፣ ምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ሰከላ ወረዳ፣ በግሽ ቀበሌ ከግሽ ተራራ ስር ነው የሚመነጨው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የዓባይ መነሻ ለዓመታት ያወዛግብ ነበር፡፡ በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ስኮትላንዳዊው ምድር አሳሽ ጀምስ ብሩስም የዓባይ ምንጭ ግሽ ዓባይ መኾኗን መመስከሩ ይነገራል፡፡
በአጼ ሱሰንዮስ ዘመነ መንግሥት አቡነ ዘርአብሩክ የተባሉ የሃይማኖት አባት በቦታው ይኖሩ ነበር። በሃይማኖታቸው ምክንያትም የንጉሥ ወታደሮች ሊይዟቸው በተቃረቡ ጊዜ የሃይማኖት መጽሐፍቶችን ከጥፋት ለማዳን ወደምንጯ በመጨመር መደበቃቸው በታሪክ ይነገራል፡፡
ከሰባት ዓመታት የእስር እና የግዞት ጊዜ በኋላም ተመልሰው በግዕዝ የሰጠሁሽን መጽሐፍት ስጪኝ (ትፊ ወይም ግሽ) በማለት በበትር መምታታቸው እና ምንጯም መጽሐፍቶቹ ሳይበላሹ መለሰች (ተፋች) ይላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት “ግሽ ዓባይ” ተብላ መሰየሟ ነው የሚነገረው፡፡
ምንጯ በአጠገቧ በሚገኘው የአቡነ ዘርአብሩክ ቤተክርስቲያን ስምም ፈዋሽ ጸበል እንደኾነች ስለሚታመንበት የሃይማኖት ቱሪዝም መናኸሪያም ናት፡፡
በየወሩ የሚከበረው የአቡነ ዘርአብሩክ ዓመታዊ የንግሥ በዓሉ ጥር 13 ቀን ነው፡፡
የሰከላ ወረዳ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ስመኝ ይዘንጋው የዓባይን ምንጭ ግሽ ዓባይን እና የአቡነ ዘርአብሩክ ዓመታዊ በዓልን ተፈጥሮ፣ ሃይማኖት እና ታሪክ በማስተሳሰር ለቱሪስት መስህብነት እየተሠራበት መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ይህንን ተፈጥሯዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ቦታ በማክበር ብሎም በመዘከር ሕዝቡ እውነተኛውን የዓባይ መነሻ እና ታሪኩን እንዲያውቅ እንዲሁም የቱሪስት መስህብ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ከባሕር ወለል በላይ 2 ሺህ 800 ሜትር ከፍታ ላይ በሚገኘው የግሽ ዓባይ ከተማ ዙሪያም የተለያዩ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ መስህቦች ይገኛሉ፡፡
ለመዳረሻው መንገድ፣ መብራት፣ ውኃ፣ ሱቆች፣ ሆቴሎች እና ሌሎችም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት መኖራቸውን ነው የጠቀሱት፡፡ ይህም ለመንፈሳዊ እና ታሪካዊ ምርምሮች አመቺ ነው፡፡
በዚህ ዓመት በዓሉ ለስምንተኛ ጊዜ እየተከበረ ሲኾን አከባበሩም ተፈጥሯዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ይዘቱን በሚገልጽ መልኩ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
