የንግድ ሥርዓቱን የሚያዘምኑ ጠንካራ ሀገራዊ ሥራዎች ተከናውነዋል።

12
ደሴ: ጥር 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር በአይነቱ እና በመጠኑ የመጀመርያ ደረጃ የኾነ ዘመናዊ እና ኹሉን አቀፍ የግብይት ማዕከል አስመርቋል።
120 ሚሊዮን ብር ወጭ ተደርጎበት ዛሬ የተመረቀው የገበያ ማዕከሉ አምራቹን እና ሸማቹን በቀጥታ ያገናኛል ተብሏል።
የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ታስቦ የተሠራው ባለ ሁለት ደረጃ የግብይት ማዕከል ለኀብረተሰቡ ጉልህ ጠቀሜታ አለው ነው የተባለው።
በማዕከሉ ምረቃ ላይ የኢፌዴሪ ንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር)፣ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሙሐመድአሚን የሱፍን እና ሌሎችም የዞን እና የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በምርቃት መርሐግብሩ የኮምቦልቻ ከተማ ከንቲባ መሐመድአሚን የሱፍ ኮምቦልቻ ከተማ ለንግድ እና ኢንቨስትመንት የሰጠችው ትኩረት ከፍተኛ ነው ብለዋል። ይህ የግብይት ማዕከሉ በክልሉ እና በከተማ አሥተዳደሩ በጋራ በጀት የተሠራ ሲኾን ለሕዝቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርት ማቅረብ ዋና ዓላማው ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር) በበኩላቸው ደሴ እና ኮምቦልቻን ጨምሮ በክልሉ እየተሠሩ ያሉ የገበያ ማረጋጊያ ማዕከሎች የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው አስረድተዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) በኮምቦልቻ ከተማ ገበያን እና ገበያተኛን ለማስተሳሰር የተሠራው ሥራ የሚበረታታ ነው ብለዋል። ለገበያ መረጋጋትም የማዕከሉ መሠራት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም ጠቁመዋል።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ.ር) የንግድ እንቅስቃሴው ቀልጣፋ እንዳይኾን ያደረገውን የንግድ ሥርዓት ሥብራት ለማስተካከል እና ጤናማ የንግድ ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሠራ መኾኑን አመላክተዋል።
የግብይት ማዕከላት ሸማች እና ገዥን በቀጥታ የሚያገናኙ በመኾናቸው ፋይዳቸው የላቀ ነውም ብለዋል።
የንግድ ሥርዓቱን ለማዘመን እና ዲጂታላይዝድ ለማድረግ ጠንካራ ሥራዎች መከናወናቸውንም ጠቁመዋል።።
የቅዳሜ እና እሑድ የገበያ ማዕከላት በየቦታው ለማስፋት የተሠራ ቢኾንም በከተሞች የግብይት ማዕከላትን በመገንባት ከእሑድ እስከ እሑድ መገበያየት እንዲቻል እያደረግን እንገኛለን ብለዋል።
ዛሬ የተመረቀው ዘመናዊ የግብይት ማዕከል ውጤታማ እንዲኾን የክልሉ መንግሥት እና ከተማ አሥተዳደሩ ላከናወኑት ተግባር ምሥጋና ይገባቸዋል ብለዋል ሚኒስትሩ።
ዘጋቢ:- ሳሙኤል ኪሮስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየዓለማችን ረጅሙን እና ገነትን የሚያጠጣውን ወንዝ መነሻ ፍለጋ!
Next articleግሽ ዓባይ – ወላዲት ዓባይ