
ባሕር ዳር: ጥር 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በመጽሐፍ ቅዱስ ኦሪት ዘፍጥረት ላይ “ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከኤደን ይወጣ ነበር” ተብሎ እንደተጻፈው የኤዶም ገነትን ከሚያጠጡ አራት ወንዞች መካከል ግዮን አንዱ ነው።
“የሁለተኛው ወንዝ ስሙ ግዮን ይባላል፤ እሱም የኢትዮጵያን ምድር ይከብባል” በሚል ከወንዞቹ መካከል አንዱ ስለኾነው ግዮን ስለ ዛሬው ዓባይ መጽሐፍ ቅዱስ ያትታል።
ግዮን በሥነ ፍጥረት ተመራማሪዎች፣ በሥነ መለኮት ሊቃውንት እና በሳይንስ ጠበብቶች አድናቆት ተችሮታል። መንፈሳውያን አበውም የረቀቀ ምስጢራትን ያሜሴጥሩበታል።
ግሽ ዓባይ ደግሞ በሰከላ ወረዳ የምትገኝ የታላቁ የግዮን ወንዝ መነሻ እና የታሪክ ማኅደር ናት። በዚች ምድር ታሪክ ተከትቦባታል፣ ሥርዓት ተመሥርቶባታል፣ ምስጢር ተገልጦባታል፤ ተዓምር ተሠርቶባታል፣ ለጻድቃን ማደሪያ ኾና ተጸልሎባታል፣ የፈውስ ቃልኪዳን ተገብቶላታል። እስከ ዛሬዋ ዕለትም ቃልኪዳኑን እያሰቡ በርካቶች ይጎርፉሉ።
ግሽ ዓባይ ስያሜዋን ያገኘችውም በጻዲቁ አቡነ ዘር ዓቡሩክ እንደኾነም ይገለጻል። አቡነ ዘር ዓቡሩክ የተባሉት አባት በዚች ስፍራ እየጸለዩ፣ ወንጌል እየሰበኩ ይኖሩባት እንደነበር በገድላቸው ተገልጿል።
የጽድቅ ሥራቸውን ያልወደዱት በዘመኑ የነበሩት ንጉሥ ሊያስሯቸው በፈለጓቸው ጊዜ ከራሳቸው ይልቅ ለጸሎት መጽሐፎቻቸው አብዝተው ተጨነቁ። የንጉሱ ጭፍሮችም ወደ እስር ቤት ሊወስዷቸው ሲመጡ መጻሕፎቻቸውን ለግዮን ወንዝ አደራ ሰጡ፣ ወደ ጊዮን ምንጭም ጨመሩ።
ከዓመታት በኋላ ከእስር ቤት ሲመለሱ “ኦ ግዮን ግሥኢ መፃሕፍትየ” “ግዮን ሆይ መጽሐፎቼን ግሽ” አሏት። ግሽ ማለት በግዕዝ ትፊ ወይም አውጭ እንደማለት ነው።
በዚህ ጊዜ አቡነ ዘር ዓቡሩክ በዓባይ ምንጭ ውስጥ ያስቀመጧቸው መጽሐፎች አንዳችም እርጥበት ሳይኖራቸው በደረቅ ስፍራ እንደተቀመጡ ኾነው አገኟቸው።
አብሯቸው የነበረው ደቀ መዝሙርም በሚያየው ተአምር በመደነቁ መጽሐፎቹን ለአቡነ ዘር ዓቡሩክ እያሳየ “አባ ዕይ” አላቸው። ከዚህ መነሻነትም የዓባይ መነሻ የኾነችው የግዮን ምንጭ ስፍራ ግሽ፣ አባ እና ዕይ ከተባሉት ሦሥት ቃላት “ግሽ ዓባይ” የሚለውን ስያሜ እንዳገኘች ይገለጻል።
አቡነ ዘርዓቡሩክም የሰጡት አደራ በተዓምር ተጠብቆ በማግኘታቸው የግዮን መንጭ የኾነችዋን ቦታ ባርከዋታል። በመጨረሻም ጥር 13 ቀን አርፈዋል።
የአቡነ ዘርዓ ቡሩክ ዓመታዊ ክብረ በዓል በግሽ ዓባይ ለበርካታ ዓመታት በሃይማኖታዊ ሥርዓቱ እየተከበረ ዘልቆ ለዚህ ትውልድ ደርሷል። በተለያየ ጊዜ ቦታውን የረገጡ ጎብኝዎችም የፈውስ ምድር ስለመኾኗ ይገልጻሉ፡፡
ዛሬም በርካታ እንግዶች በአቡነ ዘርዓብሩክ ጸበል መፈወስን የሚሹ የሃይማኖቱ ተከታዮች በብዛት ወደ ስፍራው ያመራሉ። ከሩቅ ያሉ ጎብኝዎችም የዓለማችን የረጅሙን ወንዝ መነሻ፣ ገነትን የሚያጠጣውን ወንዝ መወለጃ ስፍራ ለማየት ይጓዛሉ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ግዮን ለቱሪዝም እንቅስቃሴ ያለውን ሃብት ታሳቢ በማድረግ እና የአቡነ ዘርዓ ብሩክ ዓመታዊ ክብረ በዓል በማስተሳሰር ከፍ ባለ ደረጃ “ግዮንን በግዮን” በሚል መሪ መልዕክት እየተከበረ ይገኛል።
በዚህ በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስትያን በያሬዳዊ ዝማሬ፣ በቅኔ እና በሌሎችም ሃይማኖታዊ ክዋኔ ግዮንን እና አቡነ ዘርዓ ቡርክን ያወድሳሉ፣ ምሥጋናም ያቀርባሉ።
የማኀበረሰቡ ቱባ ባሕልም እንዲሁ በአደባባይ ይደምቃል። ባሕላዊ አልባሳት ይለበሳል፣ የፈረስ ጉግስ ይከናወናል፣ ወጣቶች ይጨፍራሉ፣ አባቶች እና እናቶች በእልልታ እና በሆታ ታቦቱን ያጅባሉ።
ጊዮን የፈለቀባት ያቺ የተቀደሰች ምድር ዛሬም ደምቃ ትውላለች።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
