የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ52ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።

20
ባሕር ዳር: ጥር 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 52ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡
1. በቅድሚያ ምክር ቤቱ የተወያየው የጉምሩክ አዋጅን እንደገና ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ በሥራ ላይ ያለው የጉምሩክ አዋጅ ለበርካታ ዓመታት ያገለገለ በመሆኑ፣ የአዋጁን ድንጋጌዎች ዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ጋር ለማጣጣም፣ በአገራችን እያደገ የመጣውን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ለመደገፍ፣ እንዲሁም ሕጋዊ ንግድንና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ይቻል ዘንድ የማሻሻያ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በማሻሻያ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል አዋጁ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡
2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው ለኢንቨስትመንት ስለሚሰጥ የታክስና ቀረጥ ማበረታቻ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ ለሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላላቸውና ቅድሚያ ለሚሰጣቸው፣ እንዲሁም ከፍተኛ ካፒታል ለሚጠይቁ የኢንቨስትመንት መስኮች በሥራ ላይ የሚውለውን ካፒታል ከግምት ውስጥ የሚያስገባና በአፈጻጸም ላይ የተመሠረተ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል፣ ደንቡ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡
3. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ነው፡፡ ፖሊሲው በኢንተርፕረነርሽፕ ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራት ቀጣይነት ኖሯቸው ለሀገራዊ የልማት ግቦች ስኬት ሚናቸውን እንዲወጡ፣ የፈጠራ ባህልን ለማጎልበትና እሴትን ለመጨመር የሚያስችል ምቹ የኢንተርፕረነርሽፕ ሥነ-ምህዳር ለመገንባት እንዲቻል ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል፣ ፖሊሲው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከጸደቀበት ከጥር 12 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡
መረጃው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየዘገሊላ ‘ለት የዘገሊላ ‘ለት ነይልኝ በኔ ሞት።
Next articleበኩር፡ 30ኛ ዓመት ቁጥር 6 ጥር 11 ቀን 2018 ዓ. ም