የዘገሊላ ‘ለት የዘገሊላ ‘ለት ነይልኝ በኔ ሞት።

13
ባሕር ዳር: ጥር 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕል አምባሳደሩ ድምጻዊ ይሁኔ በላይ ”የዘገሊላ’ለት” በተሰኘው ሙዚቃው በኢትዮጵያ የጥር ወር ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ መሥተጋብሮችን በድንቅ የትወና ችሎታው ታጅቦ ይነግረናል።
የዘገሊላ ‘ለት የዘገሊላ ‘ለት
ነይልኝ በኔ ሞት።
የአስተርዮ ማርያም… የአስተርዮ ማርያም
እመጣለሁ እኔም።
ባል ነው… ባል ነው… ባል ነው… ባል ነው፤
ብንገናኝ ምነው… ዓለም ባል ነው፤
በማለት እያቀነቀነ በቃና ዘገሊላ በዓል መነሻነት ጥርን በሙሉ የሚከወኑ ባሕላዊ የፍቅር ጨዋታዎችን በዓይነ ህሊናችን ያስቃኘናል። በምድረ ጎጃም ያለውን የወጣቶችን የበዓላት ጨዋታ፣ ፍቅርና መነፋፈቅ ይነግረናል።
የዘገሊላ’ለት አይቸሽ ደግሜ፤
የአስተርዮ ማርያም ጸናብኝ ህመሜ፤
በማለትም ጥር የደስታ፣ የፍቅር የመውደቅ እና የመታመም መኾኑንም እየነገረን ሳይታወቀን ሙዚቃው ያልቅብናል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቃና ዘገሊላ በዓል ጥር 12 ይከበራል። በዕለቱም የሚካኤል ታቦት ይከብራል። ከዚሁ በዓል ጋርም የቃና ዘገሊላ ተዓምር መታሰቢያ ነው።
ስለዘገሊላ በዓል ማብራሪያ የሰጡን መጋቢ ምሥጢር ስማቸው ንጋቱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ በመጋቢት ወር በእስራኤል የገሊላ የባሕር ዳርቻ በቃና ተገኝቶ እንደነበር ይጠቅሳሉ።
በሰርጉ ተገኝቶ ደጋሾቹ የወይን ጠጃቸው አልቆባቸው ሲቸገሩ ባየ ጊዜ ጋኖችን ውኃ አስሞልቶ ወደ ወይን የቀየረበትም መኾኑን አብራርተዋል።
የመጀመሪያው ተዓምርም በመኾኑ ይከበራል፤ ነገር ግን መጋቢት የጾም ወር በመኾኑ ወደ ጥር 12 ተቀይሯል ብለዋል።
በቀኖና ቤተ ክርስቲያን በዓላት የደስታ በመኾናቸው በጾም ጊዜ አይከበሩም። በመኾኑም የውኃን በዓል ከውኃ ጋር ለማክበር የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጥር 12 እንዲከበር መወሰናቸውን ተናግረዋል።
ጎጃም ውስጥ ቃና ዘገሊላ የሚባል ቦታ ወይም ቤተ ክርስቲያን ያለ እስኪመስለን ድረስ ጥርን በዜማ መግለጽ ከፈለግን የዘገሊላ’ለት ዜማ ከነትዝታ ቀስቃሽ ትዕይንቶቹ በአዕምሯችን ይመጣል።
የኢትዮጵያውያን የማንነት መገለጫ ከኾኑት ሃይማኖታዊ በዓላት ውስጥ አንዱ የቃና ዘገሊላ በዓል በመላው ኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ይከበራል። ወይን ጠጃቸው አልቆባቸው ተጨንቀው ለነበሩት ደጋሾች ጋኖቻቸውን በወይን ጠጅ ስለሞላላቸው በደስታ ተንበሸበሹ። በዚህ ተዓምራት ምክንያትም እነኾ በየዓመቱ ጥር ወር የሰርግ፣ የደስታ እና የአብሮነት ወር ኾኖ ይሰነብታል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“እጣን እጣን ይሸታል መሬቱ (2) ጌታየ መድኅኔ የወረደበቱ”
Next articleየሚኒስትሮች ምክር ቤት በ52ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።