
ባሕር ዳር: ጥር 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በገና ለእግዚአብሔር ምስጋና የሚቀርብበት መሣሪያ ነው፡፡ በጥምቀት ጊዜ ደግሞ በገና ደርዳሪዎች ታቦታትን አጅበው ሲታዩ ለበዓሉ የተለየ ድባብን ይፈጥራል፡፡
ለመኾኑ በገና እና ጥምቀት ግንኙነታቸው ምንድን ነው?
በባሕር ዳር ከተማ የቅዱስ ያሬድ መንፈሳዊ የበገና ማሠልጠኛ ተቋም መሥራች እና መምህር ሊቀ መዘምራን ጌታቸው ብርሃኑ በገና ማለት የቃሉ ትርጉም መዝሙር ወይም ምስጋና ማለት ነው አሉን።
በገና እግዚአብሔርን በሰማይ መላዕክት፣ በምድር የሰው ልጆች የሚያመሰግኑበት መሣሪያ ነው ብለዋል። በገና ጥንታዊ የኾነ ከክርስቶስ ልደት በፊት ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔርን ያመሰግንበት የነበረ መሣሪያ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡
በገና እና ጥምቀት ያላቸው ትስስር የመጣው በገና ከታቦት ጋር ባለው ግንኙነት ምክንያት መኾኑን አንስተዋል፡፡ በብሉይ ኪዳን ታቦተ ጽዮን በበገና ታጅባ እንደምትንቀሳቀስ እና በየዕለቱም ምስጋና እንደሚቀርብ አስረድተዋል፡፡
ቅዱስ ዳዊት በገናን እየደረደረ ስለ ድንግል ማርያም እና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ እና መጠመቅ ትንቢት የተናገረበት ነው ብለዋል፡፡
በሐዲስ ኪዳን በጥምቀት ታቦታት ወደ ባሕረ ጥምቀት ሲወርዱ እና ምዕመኑን ባርከው ሲመለሱ በበገና ታጅበው ምስጋና እንደሚያቀርቡ ነው የገለጹት፡፡ በበገና ለእግዚአብሔር ምስጋና ማቅረብ ጥንታዊ እና የቆየ ነው፤ አሁንም በጥምቀት እንደ ጥንቱ ታቦታት በበገና እየታጀቡ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በገናን ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ ይዛው የቆየችው የንዋየ ቅዱሳት ሃብቷ ነው ብለዋል፡፡ በገና የቤተ ክርስቲያኗን ሃይማኖታዊ ምስጢራት ጨምሮ የያዘ የማመስገኛ መሣሪያ እንደኾነም ነው የገለጹት፡፡
የበገና ስሪቱም ኾነ ምሳሌው ከላይ ያለው ቀንበር እና ከታች ያለው መወጠሪያ የሰማያት እና የምድር ምሳሌ ነው ብለዋል፡፡
የድምጽ ሳጥኑ የድንግል ማርያም፣ አስሩ አውታሮች የአስርቱ ትዕዛዛት፣ በቀኝ እና በግራ የሚገኙት ሁለት ምሰሶዎች የብሉይ ኪዳን እና የሐዲስ ኪዳንን እና ከውስጥ ያለችው እንዚራ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌዎች መኾናቸውን ነው የገለጹልን።
በቤተ ክርስቲያኗ ሁሉም ነገር ትርጓሜ ተሰጥቶት እንደሚሠራ እና ዜማውም ከምስጢሩ ጋር አብሮ የሚሔድ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡ በገና የክርስቶስ መወለድ እና መጠመቅ እንደ ትንቢቱ የተገለጸበት መሣሪያ እንደኾነም አብራርተዋል፡፡
ጎልቶ ወጥቶ ጥቅም ላይ የዋለው ባለ10 አውታር በገና ነው፤ ነገር ግን 150 አውታሮች ያሉት ቅብል ቃና የሚባለው በገና በቤተክርስቲኗ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ አሁን ጥቅም ላይ የሚውለው በገና እንዚራ የሚባለው እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡
የበገና ዕውቀቱን ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር በሰፊው እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ በዘንድሮው የጥምቀት በዓል በባሕር ዳር ከተማ ከ500 በላይ በገና ደርዳሪዎች ታቦታትን ያጅባሉ ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
ከቤተ ክርስቲያኗ ትውፊት እና ሥርዓት ሳይወጡ በገናን በአግባቡ ተምሮ መጠቀም ያስፈልጋል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በገና ደርዳሪ ዲያቆን ማናየ አሌ ለጥምቀት በዓል በበገና ምስጋና ለማቅረብ እና ታቦታትን ለማጀብ በርካታ በገና ደርዳሪዎች ዝግጅት እያደረጉ መኾኑን ነግሮናል፡፡
በገና መደርደር ከሃይማኖታዊ አገልግሎት በተጨማሪ መንፈስ እንዲታደስ የሚያደርግ እና ለተጨነቁ ሰዎች ሰላምን እና እረፍት እንደሚሰጥም ገልጾልናል፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
