
ፍኖተ ሰላም: ጥር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል መንግሥት እና በአፋሃድ መካከል ኅዳር 25/2018 ዓ.ም የተፈጠረውን የሰላም ስምምነት መሠረት በማድረግ በምሥራቅ ጎጃም ዞን በባሶ ሊበን ወረዳ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ21 በላይ የታጠቁ ኀይሎች የሰላም አማራጩን ተቀብለው ወደ መንግሥት እና ሕዝብ ተመልሰዋል።
ታጣቂዎቹ 11 ክላሽ፣ ሁለት ዲሽቃ፣ ሁለት ስናይፕር፣ 53 የዲሽቃ እና 52 የብሬን ጥይት እንዲሁም ሌሎችንም የጦር መሳሪያዎች በመያዝ ነው የሰላም አማራጭን የተቀበሉት።
ታጣቂዎቹ ገብተውበት የነበረው ትግል ዓላማውን የሳተ እና የሀገርን ሉዓላዊነት አሳልፎ የሚሰጥ በመኾኑ የመንግሥትን የሰላም ጥሪ እና ስምምነት በመቀበል መምጣታቸውን ተናግረዋል።
ታጥቀው በጫካ የሚንቀሳቀሱ ሌሎች ወገኖችም ዕውነታውን ተረድተው የሰላም አማራጭን በመቀበል ማኅበረሰቡ ላይ እየደረሰ ያለውን እንግልት ሊቀንሱ እና ሊክሱ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ዋለ አባተ የሰላም ስምምነቱን ተቀብለው የገቡ የታጠቁ ኃይሎች እንቅስቃሴያቸው የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥል እና በክልሉ ሕዝብ ያስከተለውን ጉዳት በመገንዘብ ትግሉ ያልተገባ መኾኑን ተገንዝበው የመጡ ናቸው ብለዋል።
ሌሎችም የታጠቁ ኃይሎች የሌሎች ኃይሎች መጠቀሚ እንዳይኾኑ የሰላም መንገድን የመረጡ ታጣቂዎችን ፈለግ ተከትለው እንዲመጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዋና አዛዥ ብርጋዴል ጄኔራል ሶፍያ መሐመድ ዛሬ ወደ ሰላም የመጡ ኃይሎች በተለያየ መንገድ ወደ ጦርነት የገቡ ቢኾንም አሁን ላይ ከክልሉ አልፎ ሀገርን ለጠላት አሳልፎ ከሚሰጥ ትግል ውስጥ አንገባም ብለው የመጡ ናቸው ብለዋል።
ሌሎችንም ኃይሎች በንግግር እና በስምምነት ወደ ሰላም እንዲመጡ እየተሠራ መኾኑን አስገንዝበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
