“ጥምቀት ፍቅርን፣ መተሳሰብን እና መደማመጥን ያስተምራል” ብጹዕ አቡነ አብርሃም

6

ባሕር ዳር: ጥር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል በባሕር ዳር ከተማ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች እየተከበረ ይገኛል።

 

በዓባይ ማዶ ጥምቀተ ባሕር እየተከበረ በሚገኘው የጥምቀት ሥነ ሥርዓት ላይ የባሕር ዳር እና የሰሜን ጎጃም አሕጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ አብርሃም ለምዕመኑ ቡራኬ ሰጥተዋል።

 

የጥምቀት በዓል በመጽሐፍ ቅዱስ ስማቸው ከተጠቀሱት ከአራቱ አፍላጋት መካከል አንዱ በኾነው ዓባይ ወይም ጊዮን ወንዝ ዙሪያ ማክበራችን ታሪካዊ ይዘት ያለው ነው ብለዋል ብጹዕነታቸው።

 

“ጥምቀት ፍቅርን፣ መተባበርን፣ መደማመጥን እና መከባበርን ያስተምራል ብለዋል። ጭፈራውን እና ሃይማኖታዊ ክዋኔውን ሳይቀላቅሉ በሥርዓት ማክበር እንደሚገባም በዕለቱ አሳስበዋል። ሃይማኖታዊ በዓላት ሃይማኖታዊ ይዘትን በጠበቀ መልኩ መከበር እንደሚገባቸው ነው የገለጹት።

 

በጥምቀት በዓል ሀገርን የሚያወድሱ መዝሙሮች የሚዘመሩበት፣ እግዚአብሔር የሚመሰገንበት፣ ታዛዥ ኾኖ በፍቅር የሚመላለሱበት መኾኑን ተናግረዋል። ከአባቶቻችን እና ከእናቶቻችን የተቀበልነው ትውፊትም ይህ ነው ብለዋል።

 

በዓሉን እግዚአብሔር ለችግራችን መፍትሔ እንዲሰጠን በመለመን መኾን እንደሚገባም ገልጸዋል። ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለ ይቅርታ ስለ ምህረት የምንማጸንበት፣ ለተቸገሩት የምናስብበት መኾኑን ልብ ሊባል እንደሚገባም አሳስበዋል።

 

ጊዜው የሚጨፈርበት ሳይኾን እግዚአብሔር ምሕረቱን እንዲልክልን የምንጸልይበት ነው ብለዋል ።

 

እግዚአብሔር የሰጠንን ሕግ በመፈጸም እና በተግባር ያስተማረንን አክብረን ተዛዝኖ እና ተሳስቦ መኖር እንደሚገባ ነው የገለጹት።

 

ብጹዕነታቸው ቡራኬ ሰጥተው ሥርዓተ ጥምቀቱ የተከናወነ ሲኾን ሌሎች ልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች ቀጥለዋል።

 

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጥምቀት በዓል በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልንበት ልዩ በዓላችን ነው” 
Next article”በጥምቀቱ የተራራቁት ተቀራረቡ፤ የተጣሉት ታረቁም” ብጹዕ አቡነ ዘካርያስ