
ባሕር ዳር: ጥር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል በጎንደር ከተማ እየተከበረ ይገኛል። በዓሉ ከፍተኛ የመንግሥት መሪዎች እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አባቶች የታደሙበት ነው።
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብ ምዕራብ ሽዋ እና የሸገረ ከተማ አሕጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አሥኪያጅ ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ ጥምቀትን ለማክበር በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ ለተገኙ እና ለመላው የሃይማኖቱ ተከታዮች ኢትዮጵያውያንን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዓለ ጥምቀት የመገለጥ በዓል ነው፤ ታላቁ ምስጢረ ሥላሴ የተገለጠበት ነውና ብለዋል። የጌታችን ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ በመሄድ በዮሐንስ እጅ መጠመቁም ለማኅበራዊ ሕይዎታችን ጭምር ትምህርት የሚሰጥ ትልቅ ትህትና የተገለጠበት ስለመኾኑ ጠቁመዋል።
ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ ጥምቀት የአንድነት እና ያለመለያየት ምስጢርን የያዘ በዓል ስለመኾኑም አስተምረዋል። ይህ ታላቅ እና ታሪካዊ በዓል በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ መከበሩም ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
ጎንደር በታሪካዊ ቅብብሎሽ ሀገር የገነቡ እና ለቤተክርስቲያን አንድነት ጉልህ ሚና የተወጡ ታላላቅ ነገሥታት የመሠረቷት እና ያሳደጓት ከተማም ናት ብለዋል። ጥንታውያን አድባራት እና ገዳማት እንዲሁም በ17ኛው እና 18ኛው ክፍለ ዘመን የተሠሩ ታሪካዊ ቅርሶቿ ለጎንደር ትልቅነት ምስክሮች መኾናቸውንም ገልጸዋል።
“ጎንደር ስማቸው በታሪክ የሚነሳ ታላላቅ ሊቃውንት የነበሩባት እና ዛሬም የሚገኙባት ሀገረ ጥበብ እና ሀገረ አዕምሮ ናት” ብለዋል አቡነ ሳዊሮስ። በቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ እና በሌሎችም ጉባኤያት የእድገት ታሪክ ውስጥ የጎንደር ሚና ከፍተኛ ነው፤ በመላው ሀገራችን ውስጥ በሚገኙ አድባራት እና ገዳማት የሚገኙ ሊቃውንት ሁሉ ከጎንደር የተቀዳ ትምህርት እንዳላቸውም ጠቁመዋል።
ጎንደር እና የጎንደር ሊቃውንት ለትምህርት እና ለጥበብ መስፋፋት የላቀ ሚና የተጫወቱ በመኾኑ ከፍ ያለ ምስጋና እንደሚገባቸውም ገልጸዋል። ሥነ ጥበብ፣ ኪነ ሕንጻ እና ሌሎችም አበርክቶዎች የጎንደር ውለታ ከሚነሳባቸው ዘርፎች መካከል እንደኾኑም ተናግረዋል።
ይህንን የሊቃውንቱን ዘርፈ ብዙ ሚና ስናነሳ የኋላ ደጀን ኾኖ ለተማሪዎች የሚያስፈልገውን ሁሉ እያቀረበ ያስተማረ እና አሁንም ይህንን ባሕሉን ጠብቆ ያለውን የጎንደር ሕዝብንም ማመስገን እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።
የጎንደር ታሪክ እና ጥበብ ሳይደበዝዝ ሊቀጥል እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሊቃውንት የጥበብ መንገድ ለጠፋው ሁሉ ብርሃን ልትኾኑ ይገባል ያሉት ብጹዕነታቸው የሀገራችን ችግሮች በሙሉ ተወግደው ወደ ከፍታ እንድትጓዝ ሁሉም የበኩሉን አበርክቶ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ፍቅር እና አንድነትን ከመሻት ይልቅ ወደ ጸብ እና ክርክር ማዘንበል የለብንም፤ ይህ ምስጢር በጠፋብን ጊዜ ሊቃውንቱ ረቂቅ ምስጢራቱን የመፍታት፣ የማስተማር እና የመምከር ኀላፊነት አለባቸው ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
