
ባሕር ዳር: ጥር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በጎንደር ቅዱስ ፋሲለደስ ጥምቀተ ባሕር እየተከበረ ነው፡፡ በበዓሉ ላይ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴን ጨምሮ የፌደራል እና የክልል የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ ጥምቀት በተለይም በጎንደር በድምቀት የሚከበር ታላቅ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓል መኾኑን አንስተዋል፡፡ ጎንደር የጥበብ፣ የዕውቀት እና የደግነት ከምንም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያዊነት ምስክር የኾነች ከተማ ናት ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህ የጎንደር እናትነት ከሚገለጥባቸው ሁነቶች አውራው ጥምቀት እንደኾነ ጠቁመዋል፡፡
ዛሬም እንደ ትናንቱ ጥምቀትን በጎንደር ለመታደም ከሀገር ውስጥም ኾነ ከባሕር ማዶ የመጡ የጎንደር እንግዶችን “እንኳን ተገናኘን” ብለዋቸዋል፡፡ የጎንደር ሕዝብ እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰው እና ሀገር ወዳድ፣ አስተዋይ እና የተረጋጋ ሕዝብ እንደኾነ ያነሱት ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በጀግንነት ውስጥ ጎልቶ የሚስተዋለው ቻይነቱም ለአብሮ መዝለቅ ምሰሶ እና ማገር ኾኖት እንደቆየ አንስተዋል፡፡
“በዚች ከተማ ያልተመላለሱ ነገሥታት፣ አሳሾች እና አጥኝዎች አልነበሩም” ያሉት ፕሬዝዳንቱ ነገር ግን ሁሉም አልፎ ሂያጅ እንጅ አስተዋይ አልነበሩም ብለዋል፡፡ ዛሬ ጎንደር የመታደሷ ዘመን ላይ ነች ስንልም ያለምክንያት አይደለም ነው ያሉት፡፡ የስንፍናችን እና የመቆዘማችን ምልክቶች የነበሩት የጎንደር ጥቀርሻ እና አቧራ ተራግፈው መታደሰ ላይ መኾናቸው አንድ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ለጎንደር መታደስ በጎንደር ከማለፍ ይልቅ ጎንደርን በማስተዋል ያዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና በጎንደር አብያተ መንግሥታት ጥገና እና እድሳት ድርሻ እና አበርክቶ የነበራቸውን ሁሉ ፕሬዝዳንቱ አመስግነዋል፡፡ የጎንደር ሕዝብ የመንግሥትን ዋጋ ዛሬ ብቻ ሳይኾን ጥንትም ቀድሞ ያውቃል ያሉት ፕሬዝዳንቱ መሪ፣ ሃሳብ እና ሕዝብ ሲስማሙ ምን አይነት ተዓምር እንደሚፈጥሩ በአንድ ዓመት ያየነው ለውጥ ምስክር ነው ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በመልዕክታቸው ኢትዮጵያ ብዙ እድሎች እና የማደግ ተስፋዎች እንዳሏት እያየን ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን ሰልፋችን ከሚገሰግሱት እንጅ ከሚጎትቱት መኾን የለበትም ነው ያሉት፡፡ ሀገራችሁ ማደጓን ቀርቶ ቆማ መቀጠሏን የማይፈልጉ በርካታ ጠላቶች አሏት ያሉት ፕሬዝዳንቱ በዚህ ዘመን በጋራ መቆም ከምንጊዜውም በላይ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
