የገበታ ፕሮጀክቶች የተቀበረ ታሪክን እየገለጡ ነው።

1

ባሕር ዳር: ጥር 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አነሳሽነት በሀገር አቀፍ ደረጃ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገኘው የገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን መልከ ብዙ ገጽታ እየገለጡ ይገኛል።

ፕሮጀክቶቹ ውበት ይገለጽባቸዋል፤ እምቅ ሃብቶች በይፍ ገቢር ይኾኑባቸዋል፤ ለቱሪዝም መንሠራራት ዓይን ገላጭ ናቸው። ተደብቀው የነበሩ የተፈጥሮ ሃብቶች በአደባባይ እንዲወጡ ዕድል ይዞ የመጡ ናቸው የገበታ ፕሮጀክቶች።

የሀገር የጀርባ አጥንት የኾነውን ኢኮኖሚም በማገዝ ረገድ ሚናው ቀላል አይደለም። የሀገር ፈተና የኾነውን ሥራ አጥነትን በመቅረፍ በኩልም አንድ መፍትሔ ኾኖ የተገኘ አማራጭ ነው ማለት ይቻላል።

ሀገሪቱ በአስደናቂ ታሪኳ፣ በተለያዩ መልክዓ ምድሮች እና ህያው ባሕሏ የጉዞ መዳረሻ ኾና ይበልጥ እንድትደምቅ በማድረግ በኩልም መፍትሔ ተደርጎ በትኩረት እየተሠራበት ነው።

የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን የቱሪዝም ዕድገት ከፍ የሚያሳዩ እና በዘርፉ ያለውን ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉም ናቸው።

በአማራ ክልል ተደብቀው እና ተሸፍነው የቆዩ የቱሪዝም ሃብቶች እንዲገለጡ እና ለቱሪዝም ልማት እንዲውሉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሢሠራ ቆይቷል።

​ከ‘ገበታ ለትውልድ’ የቱሪዝም ልማት ፕሮጀክቶች መካከል በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ ከተማ አቅራቢያ ግንባታው እየተፋጠነ የሚገኘው የገበታ ለትውልድ ሐይቅ ሎጎ ሪዞርት አንዱ ሲኾን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጎርጎራ ላይ የተገነባው የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ደግሞ ዋናውና ውጤታማው ነው።

ፕሮጀክቶቹ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ትርጉም ባለው ደረጃ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፤ ለዘላቂ ልማት እና ብልጽግናም መንገድ ጠራጊ ናቸው።

የፕሮጀክቶቹ ዕውን መኾን ለአካባቢው ማኅበረሰብ ትርጉም ባለው ደረጃ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ ለዘላቂ ልማት እና ብልጽግና መንገድ አመላካች ይኾናል። የቱሪዝም አቅምን ከማጠናከራቸውም በላይ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ገጽታ በመሠረታዊነት እየቀየሩ ነው። ጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትም ለዚህ አንድ ማሳያ ነው።

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በአንድ ወቅት የሐይቅ ሪዞርትን በጎበኙበት ጊዜ ባደረጉት ንግግር የልማት ውጤቱ መልከ ብዙ ነው ብለው ነበር። በአንድ አካባቢ የሚደረግን ማንኛውንም ዓይነት ልማት ከደገፍነው እና ከተንከባከብነው አካባቢውን በአንድም ኾነ በሌላ መንገድ ይቀይራል ማለታቸው የሚታወስ ነው።

የሚሠሩ ልማቶች ዝቅ ሲል ለአካባቢው ከፍ ሲል ደግሞ ለሀገር ታሪክ ቀያሪ፤ ለውጥ ፈንጣቂ እንደሚኾኑ ነው የገለጹት። ለዚህም የገበታ ፕሮጀክቶች ህያው ምስክሮች እንደኾኑ እና በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶችን መመልከት በቂ እንደኾነ ገልጸው ነበር።

የፕሮጀክቱ ሃሳብ ጠንሳሽ የኾኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የገበታ ለሀገር አንድ አካል የኾነው የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ሲመረቅ ባስተላለፉት መልዕክት የገበታ ፕሮጀክቶች የታሪካችን፣ የመጻዒ ዕድሎቻችን እና የሕልማችን ነጸብራቆች ናቸው ሲሉ ገልጸው ነበር።

በፕሮጀክቶቹ አማካኝነት ታሪካዊ ቦታወችን ዳግም እንዲወለዱ እና እንዲታደሱ በማድረግ ወደ ነበረበት ክብር መመለስ ብቻ ሳይኾን አልቆ መታየትን የምናይበት እንደኾነም ማንሳታቸው ይታወሳል።

ብቻ የሀገር ልማት አንድ አቅጣጫ የኾነው የገበታ ፕሮጀክት ከጽንሰ ሃሳብ በዘለለ የብዙ ነገሮች አቅም እየኾነ መጥቷል። ፕሮጀክቶቹ የመልማት አቅም ግርዶሽን የገፈፉ እየኾኑም ይገኛሉ።

በሰለሞን አንዳርጌ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የፋሲለደስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ሕንፃ ግንባታ የነገ ሀገር ተረካቢዎችን ለመቅረጽ የሚያስችል ነው” አቶ መላኩ አለበል