
ባሕር ዳር: ጥቅምት 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጻጻስ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የጥምቀት በዓልን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ጥምቀት የክርስቶስ ትክክለኛ መንገድ ማሳያ ነው ብለዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ትክክለኛ መንገድ ደግሞ ፍጹም ፍቅር እንደኾነ ነው የገለጹት። ክርስቶስ የተጠመቀው ወልደ እግዚአብሄር መኾኑን ለመግለጽ እና ለሰው ልጅ መዳን ሊያበስር ስለመኾኑ በመግለጫቸው አንስተዋል።
“የኢየሱስ ክርስቶስን የጥምቀት በዓል ስናከብር ትክክለኛውን የክርስቶስ መንገድ በመከተል መኾን ይገባል” ነው ያሉት።
የጌታ ጥምቀት አዲስ ሳይኾን አስቀድሞ በነብያት የተነገረ ነው ያሉት ብፁዕነታቸው ለሰው ልጅ ምሳሌ ይኾን ዘንድ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ በመሄድ ጥምቀትን ከውኗል ብለዋል። ጥምቀትን ስናከብር ኢየሱስ ክርስቶስ የእውነት መንገድ በመኾኑ ይህንን መከተል እና መተግበር ይገባል ነው ያሉት።
በዓሉን ለማክበር ወደ ጎንደር የሚመጡ እንግዶችንም በአግባቡ ማስተናገድ እንደሚገባም በመግለጫቸው አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ኤልያስ ፈጠነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
