የግዥ ሥርዓቱን ለማዘመን እና ለማቀላጠፍ የወጣው አዋጅ አንደምታ፦

8

 

ባሕር ዳር: ጥር 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት በ6ኛ ዙር፣ 5ኛ ዓመት፣ 11ኛ መደበኛ ጉባኤው የአማራ ክልል የግዥና ንብረት አሥተዳደር ማሻሻያ አዋጅ አውጥቷል፡፡

በአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ የፕሮጀክት ከፍተኛ የግዢ ባለሙያ አቤል ጥላሁን የአዋጁን መውጣት ምክንያቶችን፣ አዳዲስ ድንጋጌዎቹን እና ጥቅሞችን አብራርተውልናል፡፡

እንደ እሳቸው ሃሳብ አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገበት ዋና ዋናዎቹ ምክኒያቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡

በሥራ ላይ የነበረው የግዢና ንብረት አሥተዳደር አዋጅ ቁጥር 179/2003 ለረጂም ጊዜ በመቆየቱ ያሉበትን የአፈጻጸም ክፍተቶች ለማረም፣ የፌደራል መንግሥት ካወጣው የግዢ አዋጅ ቁጥር 1333/2016 ጋር ለማጣጣም፣ የግዢ ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ በማገዝ እና ዲጂታላይዝድ በማድረግ ፍጥነትን፣ ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን ለማጠናከር፣ የሚገዙ እቃዎች እና ግንባታዎች የሕይወት ዘመን ትንተና፣ ዘላቂነት ያለው ግዥ ማለትም መልሶ መጠቀምን፣ አረንጓዴ ግዥ እና የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ የሚያስችል መኾኑን ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በጸደቀው የግዥና ንብረት አሥተዳደር ማሻሻያ አዋጅ የተጨመሩ፣ የተቀነሱ ወይም የተሻሻሉ ዋና ዋና ጉዳዮች፡-

👉 ግዢ በእቅድ እንዲከወን ትኩረት ሰጥቷል፤
👉 ቁጠባን ያበረታታል፤ ግልጽነትን እና ተጠያቂነትንም ያሰፍናል፤
👉 ግዢ በኮሚቴ ስለሚጸድቅ የተቋም ኀላፊ ገለልተኛ እና ነጻ ይኾናል፤
👉 ንብረትን በወቅቱ አለማስወገድ እንዲያስጠይቅ ደንግጓል፤
👉 ባለቤት የሌላቸው ንብረቶችን የገንዘብ ቢሮ እንዲኾኑ ደንግጓል፤
👉ደረጃውን ለጠበቀ እቃ ግዢ እና ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት ሰጥቷል፤
👉 በተሰበረ ወይም በተጋነነ ዋጋ አሸንፈው ሥራን የማይሠሩ ተጫራቾችን መከላከል እንዲቻል ደንግጓል፤
👉የተበጣጠሰ የግዢ መመሪያ ቀርቶ ማንኛውም የግዢ እና ንብረት አሥተዳደር መመሪያ በገንዘብ ቢሮ እንዲያልፍ ያዝዛል፤
👉በግንባታ ግዢ ላይ ዲዛይንም ግንባታንም ተቋራጩ ይወስዳል፤ የመዘግየት፣ የጥራት ጉድለት፣ ወዘተ ኀላፊነትንም ይወስዳል፤
👉በተጫራቾች የመጫረቻ ሰነድ አርትሜቲክ ስህተትን ማረም አይቻልም፤
ተቋማት በጋራ ኾነው ግዢ መፈጸም ይችላሉ፤

አዋጁ በመሻሻሉ የሚገኙ ጥቅሞች፡-
👉የሰው ንክኪን በመቀነስ ሙስናንም የሚቀንስ የግዢ ሥርዓትን ይፈጥራል፣
👉ሁሉም የግዢ ሥርዓቶች በኤሌክትሮኒክስ ሥርዓቱ እንዲያልፉ እድል ይሰጣል፤ ተደራሽነትን ያሳድጋል፤ አሳታፊነትንም ይጨምራል፤ ፍትሃዊነትንም ያሰፍናል፤
👉ስታንዳርድ (ወጥ የኾነ) የግዢ ሰነድ ስለሚዘጋጅ ግለሰብ ተወዳዳሪዎችን የሚጠቅም ሰነድ ማዘጋጀትን ያስቀራል፤
👉በኮሚቴ ስለሚሠራ እና ግዢ ስለሚጸድቅ የግለሰቦችን ውሳኔ እና ብልሹ አሠራርን ይቀንሳል፤
👉ለግዢ ሂደት የሚወጣውን የገንዘብ፣ የጉልበት እና የጊዜ ወጪ ይቀንሳል፤
👉ግዢን ከሰው እና ከወረቀት ንክኪ በመቀነስ ብልሹ አሠራርን ይከላከላል፣
👉ግዢን ለሕዝብ ግልጽ በማድረግ የአሳታፊነትና የተጠያቂነት መርህን መተግበር ያስችላል፣
👉ጥለው ይሄዱ (ይጠፉ) የነበሩ የግንባታ ተቋራጮችን ይቀንሳል፤ የግንባታዎች መጓተት ወይም መቋረጥ ይቀንሳል፤

ምንም እንኳ የግዥ ሥርዓቱን ለማዘመን እና ለማቀላጠፍ ሕጎች ቢሻሻሉም የአንድ ተቋም ወይም ግለሰብ ብቻ ኀላፊነት አለመኾኑን ነው አቶ አቤል የገለጹት፡፡

ግዢን በውጤታማነት ለመፈጸም ከሕግም ባለፈ የኅብረተሰቡን ንቁ ተሳትፎ እንደሚፈልግ ነው የገለጹት፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleለ40 ሺህ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የግብርና ብድር ሊቀርብ ነው።
Next articleበዳንሻ ከተማ አሥተዳደር የተገነቡ የልማት ሥራዎች ተመርቀው ለተጠቃሚዎች ክፍት ኾኑ።