“ካፒታል ገበያን ማቋቋም በመቻላችን ዜጎች ህልማቸው እንዳይመክን እያደረግን ነው” ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

9

 

አዲስ አበባ: ጥር 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያን አሁናዊ የኢኮኖሚ ቁመና የሚያሳይ ‘’የኢትየጵያ የፋይናንስ እምርታ” የተሰኘ ጉባኤ በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል፡፡

የጉባኤው መሪ ሃሳብ ቁልፍ አንቀሳቃሽ ተቋማት ማለትም ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ገቢዎች ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ፣ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ እና የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ከለውጡ በፊት ማክሮ ኢኮኖሚው ያጋጠመውን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ የወሰዷቸውን እርምጃዎች እና ያስመዘገቧቸውን እምርታዎች ለመድረኩ አቅርበዋል፡፡

በዕለቱ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መንግሥት ለፋይናንስ ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በትጋት ባይሠራ ኖሮ ከለውጡ በፊት አጋጥሞ የነበረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት በቀላሉ መጠገን አይቻልም ነበር ብለዋል።

ይህን ስብራት ለመጠገንም መንግሥት ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን የወሰደ ሲኾን ከነዚህም ውስጥ ለፋይናንስ መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱን ተናግረዋል።

በተቋማቱ ላይ የተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎችን የማዘመን፣ የጎደሉትን የመሙላት እና ዘመን በሚዋጁ መልኩ በመገንባታቸው በማክሮ ኢኮኖሚው እምርታ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያ ቀድሞ ሊኖራት ሲገባ ያልነበራት እና በሪፎርሙ ከተመሠረቱ ወሳኝ ተቋማት አንዱ የኾነውን የካፒታል ገበያ ሀገራዊ ጥቅም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲያብራሩ “ካፒታል ገበያ ማቋቋም በመቻላችን ዜጎች ሀሳብ ኖሯቸው በገንዘብ እጥረት ምክንያት ህልማቸው እንዳይመክን ማድረግ እየቻልን ነው” ብለዋል፡፡

የተደረገው የገንዘብ ፖሊሲ ሪፎርም የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር እና የፋይናንስ ሥርዓቱን ለማረጋጋት አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጣና በለስ የተቀናጀ ስኳር ልማት ፋብሪካ ዳግም ወደምርት ሊገባ ነው።
Next articleየክልሉን ነዋሪዎች የቤት አቅርቦት ችግር ለመፍታት እየተሠራ ነው።