ጣና በለስ የተቀናጀ ስኳር ልማት ፋብሪካ ዳግም ወደምርት ሊገባ ነው።

4

 

​ባሕር ዳር፡ ጥር 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ጣና በለስ የተቀናጀ ስኳር ልማት ፋብሪካ ያለበትን የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።

ምልከታው ፋብሪካው ያለቀትን ተጨባጭ ሁኔታ በመለየት በቁርጠኝነት ወደምርት እንዲገባ ለማስቻል ያለመ ነው።

የጣና በለስ የተቀናጀ ስኳር ልማት ፋብሪካ አጋጥመውት የነበሩ የአሠራር ችግሮችን በመፍታት ከሁለት ወራት በኋላ ወደ ሙሉ ምርት ለመመለስ ዝግጅት እያደረገ ስለመኾኑም ተገልጿል።

ፋብሪካው ካጋጠሙት ተግዳሮቶች ተላቅቆ ወደ ሥራ እንዲመለስ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በቅርበት ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የተከናወነው የተቀናጀ ጥረት ፋብሪካው ያለበትን ደረጃ አሻሽሎ ለሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ የራሱን አዎንታዊ አሻራ ማረፍ የሚችልበት ደረጃ ላይ አድርሶታል።

​የፋብሪካው የጀርባ አጥንት የኾነው የሸንኮራ አገዳ ልማት በአሁኑ ወቅት ተጠናክሮ ቀጥሏል። ከ2 ሺህ 45 ሄክታር በላይ በሚኾን መሬት ላይ የለማው አገዳ ለምርት ዝግጁ ሆኗል።

ፋብሪካው ወደ ሥራ ሲገባ በቀን ከ12 ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር የማምረት አቅም አለው። ይህም የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ የዜጎችን ፍላጎት ለማሟላት ትልቅ አቅም ይፈጥራል። አሁን ላይ የተደረሰው ዝግጅት በግብርናው እና በኢንዱስትሪው ዘርፍ መካከል ያለውን ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክር ተግባር ነው።

​በአካባቢው የሚታየው የልማት እንቅስቃሴም ፋብሪካው ወደ ምርት መመለሱን ተከትሎ ከፍተኛ መነቃቃትን እያሳየ ይገኛል። የኢንዱስትሪው ሥራ መጀመር በሚፈጥረው የገበያ ትስስር ምክንያት በጃዊ እና በፈንድቃ ከተሞች የሚገኙ የአገልግሎት ዘርፎች፣ በተለይም ሆቴሎች እና የንግድ ተቋማት ተጠቃሚነታቸው ይጨምራል።

እንዲህ ዓይነቱ ሰፊ የኢኮኖሚ መስተጋብር ለአካባቢው ማኅበረሰብ የተሻለ የሥራ ዕድል እና የተረጋጋ ገቢ የሚያስገኝ በመሆኑ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።

​የጣና በለስ የተሸናጀ ስኳር ልማት ፋብሪካ ዳግም ወደ ምርት መግባት የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ተስፋ የሚያለመልም ስኬት ነው።

ከሁለት ወራት በኋላ የሚጀመረው የተቀናጀ የምርት ሂደትም ለሀገር ሁለንተናዊ ብልፅግና መረጋገጥ በምሳሌነት የሚጠቀስ ትልቅ የልማት ምዕራፍ እንደሚኾን ይጠበቃል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፋይናንስ እምርታ በኢትዮጵያ
Next article“ካፒታል ገበያን ማቋቋም በመቻላችን ዜጎች ህልማቸው እንዳይመክን እያደረግን ነው” ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)