
ባሕር ዳር: ጥር 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የተቀናጀ የገጠር ማዕከላት የቤት እና የመሠረተ ልማት የንቅናቄ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ.ር) የቤት ልማት ፖሊሲን በመተግበር የገጠሩን ማኅበረሰብ ለማዘመን ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።
ከባለድርሻ አካላት ጋር በመምከር እና በመተጋገዝም የከተማ ቤት ችግር እንዲፈታ እንደሚሠራም ተናግረዋል። ወደ ታችኛው እርከን ሰፍቶ እንደሚተገበርም አስታውቀዋል።
የገጠር ቤት ልማት እና ምርጥ የገጠር ማዕከላትን ከገጠር ኮሪደር ልማት እና ሞዴል መንደር ግንባታ ጋር በማስተሳሰር እንደሚሠራበትም አንስተዋል።
የገጠር ቤቶች ኑሮን ለማዘመን አመቺ አይደሉም ያሉት ኀላፊው ይህንን የመቀየርም ኀላፊነት አለብን ብለዋል። የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የዘመናዊ ቤት ልማትን በውጤታማነት ማስፈጸም አካታች እና ሁለንተናዊ ብልጽግናን የማረጋገጥ አንዱ አካል መኾኑንም ገልጸዋል።
የዜጎች ኑሮ መሻሻል ከሚገለጽባቸው ውስጥ የመኖሪያ ቤት አንዱ መኾኑን ጠቅሰዋል። ጥራት ያለው እና ሰው ተኮር ዕድገት የመሻት ውጤትም ነው ብለዋል።
የሀገር ዕድገት በምን ያህል ደረጃ የኅብረተሰቡን ኑሮ እንደለወጠ መመዘን ያስፈልጋል፤ የገጠር ሽግግርን እና ከተሜነትን በዕውቀት እና በትኩረት መምራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኑሮን በከተማ ማድረግ (ክትመት) እየተስፋፋ መኾኑን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ይህንን የሕዝብ ፍልሰት የገጠር አካባቢዎችን በአግባቡ በመምራት እና በማልማት መቀነስ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የቤት አቅርቦት እና የመሠረታዊ ሸቀጦችን ዋጋ በማረጋጋት የኑሮ ውድነትን መቀነስም ፍልሰትን ለመቀነስ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
ሀገራዊ የቤት ልማት ፖሊሲ እና ክልላዊ የቤት ልማት ስትራቴጂን ተግብሮ ዜጎችን የቤት ባለቤት ማድረግ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
ስትራቴጂያዊ ፋይዳ ያለውን የገጠር እና ከተማ ቤቶች ልማት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ በመፈጸም ሕዝቡን ከቤት እጦት ችግር ለማላቀቅ እንዲሠራም አሳስበዋል።
ስትራቴጂው የሕዝቡን የቤት ችግር መፍታት እና የዘመናዊ አኗኗር ስልት ማስጀመሪያ እንደኾነም አንስተዋል። በሥራው ከሥራ ዕድል መፍጠር በተጨማሪ ለጥራት እና ዘላቂነት ትኩረት መስጠት እንደሚገባም ገልጸዋል። በትውልድ ሂደት የሚሳካውን ግብ ዛሬ እንጀምራለን ብለዋል።
ሥራውን በባለቤትነት ይዞ ለመፈጸም በይዘቱ፣ በአቀራረቡ እና በፋይዳው ተገንዝቦ መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ለሥራው የሚያስፈልጉ የመሬት፣ የገንዘብ እና የቁሳቁስ ግብዓቶችን ማሟላት፣ የባለድርሻ አካላትን ሚና አውቆ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
“የሕዝቡን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት እንቅስቃሴ ከጀመርን እና ፍላጎቱን ከቀስቀስን በኋላ ወደ ኋላ ማለት አይቻልም” ነው ያሉት። ይህንን ተልዕኮ መልቀቅ ማለት ሕዝቡን ለነበረበት የጉስቁልና ሕይወት መፍቀድ ማለት ነው ብለዋል።
በዚህ ዓመት በክልሉ በ168 ቀበሌዎች ቢያንስ አንድ የገጠር ቀበሌ ማዕከል እና በከተሞችም የቤት አቅርቦቱን ለማሻሻል እና ለማሳደግ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
