
ባሕር ዳር: ጥር 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “ሰላምን ማፅናት፣ ጸጋን ማልማት” በሚል መሪ መልዕክት በአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ እና ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ትብብር የፓናል ውይይት በባሕርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እንዳሉት የአማራ ክልል ከፍተኛ የኾነ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ጸጋ ባለቤት፣ የተማረ የሰው ኀይል እና ታታሪ ሕዝብ ያለው ክልል ነው።
ይሁን እንጂ ክልሉ ካለው ጸጋ አኳያ ማልማት ባለመቻሉ ማኅበረሰቡን ከድህነት አዙሪት ማውጣት አለመቻሉንም አንስተዋል።
ለዚህ ደግሞ ለዘመናት የዘለቀው የግጭት አዙሪት አንዱ ችግር መኾኑን ነው የገለጹት። የግጭት አዙሪቱ አሁንም ድረስ የኑሮ አካል እስከ መኾን መድረሱን አንስተዋል። ውስጣዊ ግጭቶችን የውጭ ኀይሎች የእንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ግጭት ሲያባብሱ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት በክልሉ በተከሰተው ግጭትም የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ የአካል እና የንብረት ጉዳትም ደርሷል፤ ተቋማት ወድመዋል፤ መፍናቀል ተከስቷል ነው ያሉት።
መንግሥት ከግጭቱ በፊት ችግሮችን ለመፍታት ሲሠራ መቆየቱንም ገልጸዋል። ግጭቱ ከተከሰተ በኋላም ሕግ ከማስከበር ባለፈ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት በተሠራው ሥራ በርካታ የታጠቁ ኀይሎች የሰላም አማራጭን መከተላቸውን ተናግረዋል። በተሠራው ሥራም አሁን ላይ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም መፈጠሩን አስታውቀዋል።
በግጭት እና በጦርነት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደማይቻል ያነሱት ርእሰ መሥተዳደሩ መንግሥት
አሁንም በሩን ለሰላም ክፍት አድርጎ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የክልሉን የተሟላ ሰላም ለማረጋገጥ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች እና ወጣቶች ኀላፊነት ወስደው እንዲሠሩም አሳስበዋል። በተለይም ምሁራን አሉኝ የሚሏቸውን ችግሮች በሠለጠነ መንገድ በውይይት ሊፈቱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
