
ባሕር ዳር: ጥር 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የእግር ኳስ ዳኞች ትልቅ ግምት በሚሰጣቸው ጨዋታዎች የሚፈተኑባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ።
ከእነዚህ ውስጥ ሪፈር ስፖርት የተሰኘ ድረ ገጽ ዳኞችን ይፈትናሉ ያላቸውን ኹኔታዎች ጠቁሟል።
ቅጽበታዊ ውሳኔዎችን በሚሰጡበት ወቅት፣ የሚሰጡ ውሳኔዎች ላይ ስህተቶችን የሚያርሙበት ሂደት፣ በጨዋታ ላይ በሚሰጡ ውሳኔዎች ሳቢያ ተጫዋቾች የሚያሳዩትን ስሜታዊነት ለመግራት የሚሞክሩበት መንገድ ፈታኝ መኾኑን ሪፈር ስፖርት ያስረዳል።
በፍጥነት የምታልፈው እያንዳንዷን የጨዋታ እንቅስቃሴ እንዲሁም ከዕይታ ውጭ የሚኾኑ ስህተቶችን በዳኞች አቅም ብቻ መፍትሔ ለመስጠት አስቸጋሪ ስለሚኾን ችግሩን ለመፍታት ፊፋ አዲስ ቴክኖሎጂን ታጥቄ መጥቻለሁ እያለ ነው።
ፊፋ በ2026 የዓለም ዋንጫ ላይ በዳኝነት ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል በሰው ሠራሽ አስተውሎት የታገዘ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሊያደርግ መኾኑን ቢቢሲ ስፖርት ከሳምንት በፊት በወጣው ዘገባ ይፋ አድርጓል::
በዚህ የዓለም ዋንጫ ለሁሉም ተጫዋቾች ባለ 3 አውታረ መጠን (3D) ወካይ ምስል ለማዘጋጀት ማቀዱን እና ይህም ከጨዋታ ውጭ የሚኾኑ ሂደቶችን ለመለየት እየተጠቀመ ያለውን የቴክኖሎጂ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ መኾኑንም ጠቁሟል::
ይህም ማለት በአጠቃላይ በዓለም ዋንጫው የሚሳተፉ 48 ቡድኖች ለሚኖሩት 1 ሺህ 248 ተጫዋቾች ዲጂታል የምስል ቅጂ በቴክኖሎጂው ውስጥ እንዲካተት ይደረጋል። የዲጂታል ቅጂው የሚፈጸመው ከውድድሩ በፊት እያንዳንዱ ተጫዋች ወደ አንድ የምስል ቅጂ መውሰጃ ክፍል በመግባት ይከናወናል። ይህ ሂደት አንድ ሴኮንድ የሚወስድ እንደኾነም ዘገባው አመላክቷል።
እንደ ፊፋ ገለፃ ከጨዋታ ውጭ የሚኾኑ አጋጣሚዎች ላይ ትክክለኛ ውሳኔ ለመውስድ ያስችል ዘንድ እያንዳንዱን የሰውነት ክፍል በዲጂታል ቅጂ በትክክል ቀርፆ ያስቀምጣል::
ቴክኖሎጂው ዳኞች በፍጥነት ውስጥ ባለ ሂደት እና ከዕይታ የተሸፈኑ አጋጣሚዎች ሲኖሩ ለመለየት የሚያስችላቸው መኾኑ እና የመጨረሻ ውሳኔዎችም አሳማኝ በኾነ መንገድ በምስል ማሳያ መስኮት (ስክሪን) ላይ እንደሚታይም ተገልጿል::
ቢቢሲ ስፖርት ቴክኖሎጂው በፊፋ ኢንተርኮንቲኔንታል ዋንጫ ተሞክሮ እንደነበረም አስነበቧል።
ፊፋ ከወር በፊት ኳስ ከጨዋታ ውጭ መኾኑን የሚወስን እና ባለሦስት አውታረ መጠን የምልሰት ቴክኖሎጂ እየሞከረ እንደነበር መግለጹም በዘገባው ተመላክቷል::
የፊፋ ይፋዊ ድረ ገጽ የ2026 የዓለም ቀንጫ ጨዋታዎች በሰኔ ወር ውስጥ እንደሚጀምር ያሳያል።
ዘጋቢ፦ ዘመኑ መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
