
አዲስ አበባ: ጥር 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የ20ኛ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በውጤት እንዲጠናቀቅ ላደረጉ የዕውቅና እና ሽልማት መርሐግብር አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ቀኑ ለዕውነተኛ የፌዴራሊዝም እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
የዘንድሮዉ የ20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን የኢትዮጵያ ማንሰራራት እና ሁለንተናዊ ተጨባጭ ለውጦች በተመዘገቡበት ወቅት መከበሩ ለየት ያደርገዋል ሲሉ ዋና አፈ ጉባኤው ገልጸዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ በገባበት፣ የጉባ ብስራት የኾኑ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በተጨባጭ ወደ ሥራ በገቡበት ወቅት በዓሉ መከበሩን አስረድተዋል።
በለውጡ መንግሥት ራስን በራስ ማሥተዳደር ጥያቄ ምላሽ በተሰጠበት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መከበሩ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የልማት ሥራዎች በስኬት መጠናቀቃቸውን ለማየት ማስቻሉን ዋና አፈ ጉባኤው ጠቅሰዋል።
የዘንድሮው የ20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ኢትዮጵያ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት የሚያስችላት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ በተገኘችበት ወቅት በመከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
ሰባተኛው ሀገራዊ መርጫን ለማካሄድ መንግሥት አስፈላጊውን ዝግጅቶች እያደረገ ባለበት ወቅት በመከበሩ በዓሉ ልዩ ትርጉም እንዳለውም አፈ ጉባኤው ገልጸዋል።
በዓሉ በድምቀት እና በስኬት እንዲከበር ላደረጉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች፣ የክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎች እና ርእሳነ መሥተዳድሮች፣ የሚዲያ እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ዋና አፈ ጉባኤው ምሥጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ኢብራም ሙሃመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
