
አዲስ አበባ: ጥር 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአፋር ክልል ከድንቅ ተፈጥሯዊ ሃብቶቹ ባለፈ ሕዝቡ በጽኑ የሚያከብረው “ማድኣ” የተባለ ባሕላዊ የሕግ ሥርዓት አለው። ይህ ባሕላዊ ሕግ በኢትዮጵያ፣ በጅቡቲ እና በኤርትራ ጭምር ጥቅም ላይ የሚውል ነው።።
የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ቋንቋ እና ታሪክ ምርምር ኢንሲቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሃቢብ ሙሐመድ (ዶ.ር) እንዳሉት የአፋር ባሕላዊ ሕግ “ማድኣ”ን በዩኒስኮ ለማስመዝገብ ከጅቡቲ መንግሥት ጋር በትብብር ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
በማድኣ የአፋሮች የባሕል ሕግ መሠረት ጥፋት ሲፈጸም እያዩ አለመከልከል ወይም እያዩ ማለፍ ያስቀጣል” ያሉት ዶክተር ሃቢብ በአፋር ባሕላዊ ሕግ ድርጊቱ ባይፈጸም እንኳ ሊፈጸም ታስቦ እና ታቅዶ ከነበረ እንደሚያስቀጣ ተናግረዋል።
ይህን ድንቅ ባሕላዊ ሕግ በዩኒስኮ ለማስመዝገብ የጅቡቲ እና የኢትዮጵያ ሱልጣኖች፣ የሀገር ሽማግሌዎች የመንግሥት ተወካዮች እና ልዩልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማካተት የማስመዝገብ ጥረቶች እየተደረጉ እንዳለ አመላክተዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር ዘርፍ አስተባባሪ እና የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባሕል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ ሃሚድ ዱላ እንዳሉት በባሕላዊ “ማድኣ” ሕግ አጥፊው ወይም ወንጀለኛው ሳይያዝ ወይም ሳይታሰር ቢቀርም ቅጣት ይሰጠዋል።
በዚህ ባሕላዊ ሕግ ለተፈጸመ ጥፋትም አጥፊው ብቻ ሳይኾን የአጥፊው ጎሳ በሙሉ ተጠያቂ እንደሚኾንም ተናግረዋል።
ቢሮ ኀላፊው ይህንን ሥርዓት በዩኒስኮ ለማስመዝገብ ትኩረት ያደረገ ኮንፈረንስ ከየካቲት 03/2018 ዓ.ም እስከ የካቲት 05/2018 ዓ.ም በሰመራ ከተማ እንደሚካሄድም አስረድተዋል።
የ”ማድኣ” ሥርዓት በዩኒስኮ መመዝገቡ ለሀገር ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባለፈ ቀጣናዊ ትስስር እና አብሮነትን በማጠናከር ረገድ የጎላ ሚና እንዳለውም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ሰለሞን አሰፌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
