መንግሥት የፋይናንስ ዘርፉን ከብልሹ አሠራር የፀዳ ለማድረግ ዲጂታል የግዥ ሥርዓትን ተግባራዊ አድርጓል።

14
አዲስ አበባ: ጥር 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በገንዘብ ሚኒስቴር አዘጋጅነት የፌደራል ተቋማት የመንግሥት ግዥ እና ንብረት አሥተዳደር ሥርዓት ዝርጋታ የስድስት ወራት አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ መንግሥት ከያዘው በጀት ከፍተኛው ብር ለግዥ እንደሚውል ገልጸዋል።
ውጤታማ የኾነ የግዥ ሥርዓት ለመንግሥት የበጀት አሥተዳደር ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
ዘርፉ ከፍተኛ ፋይናንስ የሚንቀሳቀስበት በመኾኑ ለብልሹ አሠራር ተጋላጭ ነው፣ በመኾኑም ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓትን መዘርጋት ይጠይቃል ብለዋል።
መንግሥት ዘርፉን ከብልሹ አሠራር የፀዳ ለማድረግ ዲጂታል የግዥ ሥርዓትን ተግባራዊ በማድረግ ዲጂታል ኢኮኖሚን ተግባራዊ እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ ተሞክሮን መነሻ በማድረግ የግዥ እና ንብረት አሥተዳደር አዋጅን መንግሥት አሻሽሏል፤ መመሪያ እና ደንቦችንም ወደ ሥራ አስገብቷል ብለዋል።
የተሽከርካሪ ስምሪት እና ቁጥጥር ሥርዓትን ለማዘመን ዘመናዊ የቁጥጥር ሥርዓት በሙከራ ደረጃ የተጀመረውን በቀጣይ በሁሉም የመንግሥት ተቋማት ተግባራዊ እንደሚኾን አስታውቀዋል።
ውስን የኾነውን የመንግሥት በጀት ለታለመለት ዓላማ ወጭ ቆጣቢ በኾነ መልኩ መጠቀሞ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በተለይም ከዋጋ በላይ እና በታች የሚቀርቡ የጨረታ ዋጋን ከተጨባጩ የገበያ ዋጋ ጋር በማመሳከር ግዥ መፈፀም እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ኢብራሂም ሙሐመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleንግድ ባንክ ወልድያ ዲስትሪክት አነስተኛ መሬት ላላቸው አርሶ አደሮች ብድር ለማቅረብ ስምምነት ላይ ደርሷል።
Next articleጥምቀትን በጎንደር ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።