
አዲስ አበባ: ጥር 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በመንፈቅ ዓመቱ እንደ ሀገር በሁሉም ተቋማት የተገኙ ውጤቶች ላይ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናታለም መለሠ ኢትዮጵያ 2018 ዓ.ም የማንሠራራት ዘመን ነው ብላ እንደጀመረች ተናግረዋል።
በ2030 አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ሀገር ለማድረግ የተሰነቀው ራዕይ ዕውን መኾኑ እንደማይቀር የታየበት ዓመት እንደኾነም ጠቁመዋል።
በአፍሪካም ኾነ በዓለም የኢትዮጵያን ታላቅነት በኩራት የሚመሰክር 110 ሚሊዮን መንገደኞችን ማጓጓዝ የሚያስችል አየር መንገድ ለመገንባት ቢሾፍቱ “አቡሴራ” ላይ የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ መቻሉን በትልቅ ስኬትነት አንስተዋል።
በኢኮኖሚው መስክ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና ራስን ከምግብ ሉዓላዊነት የተሻገረ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዘገብ የሚያስችሉ ሥራዎችን መንግሥት ሠርቷል ብለዋል።
የኑሮ ውድነትን ማሻሻል የሚያስችሉ የገበያ ትስስር እና ለኅብረተሰቡ ምርት ማቅረብ የሚያስችሉ ከግብርና እስከ ገበያ የአቅርቦት ሱቆች ውጤት ታይቶባቸዋል ነው ያሉት።
በዚህም በኢትዮጵያ ታምርት እና የበጋ ስንዴ ምርትን ጨምሮ በግብርና ሥራዎች ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የአርሶ አደሮችን ኑሮ የሚያሻሽሉ የመኖሪያ መንደሮች ሌሎች ጉልህ ሥራዎች መኾናቸውን ገልጸዋል።
ከዳንጎቴ ጋር በመኾን በ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚገነባው የአፈር ማዳበሪያ ሥራ በዓመቱ ትልቁ ሀገራዊ ሜጋ ፕሮጀክት መኾኑንም ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት በኢንደስትሪ ዘርፍ 13 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ይመዘገባል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።
የመደመር መንግሥት እንደ ጎንደር አብያተ መንግሥታት ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማደስ ለቱሪስት ፍሰቱ መጨመር ጉልህ ድርሻ ማበርከት ችሏል ብለዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ትግበራ ለከተሞች እና ለነዋሪዎች መዘመን ትልቅ አበርክቶ እንደነበረውም አስረድተዋል።
በዲፕሎማሲ መስክ ኢትዮጵያ የተሳተፈችበት የቡድን 20 አባል ሀገራት ሥብሠባ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይኾን የአፍሪካን ጥቅም ለማስከበር በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት የተደረጉ ውይይቶች ውጤታማ እንደነበሩ ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለአፍሪካውያን ባቀረቡት ጥሪ መሠረት አህጉሪቱን የሚያስተሳስር አፍሪካዊ ሚዲያ በኢትዮጵያ መፍጠር የተቻለበት ዓመት ነበር ብለዋል።
ሕዝቡ የሚጠይቃቸውን ጥያቄዎች ነቅሶ ለመፍታት በቀጣይ ስድስት ወራት ይሠራል ነው ያሉት።
7ኛው ሀገራዊ ምርጫ እና ሀገራዊ የምክክር መድረክ በዚህ ዓመት የሚጠበቁ ዐበይት ሁነቶች መኾናቸውን አስታውቀዋል።
ለሁሉም ሁነቶች ውጤታማነት ሕዝቡ የሚጠበቅበትን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
