
እንጅባራ: ጥር 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አድማስ ሁለገብ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒዬን 16 መሠረታዊ ማኅበራትን በማቀፍ በ855 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል በ1996 ዓ.ም ነው የተመሠረተው።
የኅብረት ሥራ ማኅበር ዩኒዬኑ በ 22 ዓመታት ጉዞው የአባል መሠረታዊ ማኅበራትን ቁጥር ወደ 97 ሲያሳድግ አጠቃላይ ካፒታሉም ከ253 ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷል።
ዩኒዬኑ ተልዕኮዎቹን ይበልጥ ለማሳለጥ የሚያስችሉ ከ114 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በጓንጓ ወረዳ ያስገነባቸውን ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ መጋዘኖችን ዛሬ አስመርቋል።
መጋዘኖቹ ለማዳበሪያ፣ ለእህል ማከማቻ እና ለድንች ምርጥ ዘር ማጎንቆያ አገልግሎት የሚውሉ ናቸው ተብሏል።
ዩኒዬኑ የግብርና ልማት ሥራን ለመደገፍ የተገዙ 13 የጭነት ተሽከርካሪዎችን ለአባል አርሶ አደሮች አስተዋውቋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ዩኒዬኑ የአርሶ አደሮችን ቁልፍ ችግሮች ለይቶ በመፍታት ለግብርና ልማት ሽግግር የጎላ ድርሻ እየተወጣ መኾኑንም ተናግረዋል።
የግብርና ግብዓቶችን ከማጓጓዝ ባሻገር በኢንቨስትመንት ዘርፍ በመሳተፍ ኢኮኖሚውን ለመገንባት እያደረገ ያለው ጥረትም ለሌሎች ዩኒዬኖች በአርዓያነት የሚጠቀስ እንደኾነም ጠቁመዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው ዩኒዬኑ ለአርሶ አደሮች ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ ለብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምርት እና ምርታማነት ማደግ ጉልህ ሚና እየተወጣ መኾኑንም ተናግረዋል።
ዛሬ ለምረቃ የበቁ መጋዘኖች የግብርና ግብዓቶችን ለአርሶ አደሮች በቅርበት ተደራሽ ለማድረግ እና አርሶ አደሮችን ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር እንደኾነም ገልጸዋል።
አድማስ ሁለገብ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒዬን ሥራ አሥኪያጅ መሠረት ወርቄ ዩኒዬኑ የአባል አርሶ አደሮችን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሊያቃልሉ የሚችሉ ሥራዎችን እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
የመጋዘኑ መገንባት የግብርና ግብዓቶችን ለአርሶ አደሮች በቅርበት ተደራሽ ለማድረግ ከማገዙ ባሻገር ለመጋዘን ኪራይ ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጭ የሚያስቀር ነው ብለዋል።
በዚህ ዓመት የእርሻ ሜካናይዜሽንን ለመደገፍ የሚያስችሉ 27 ትራክተሮች ግዥ መፈፀሙንም ገልጸዋል።
መንግሥት ለኅብረት ሥራ ማኅበራት የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት የማሳደግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያለት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
