
ባሕር ዳር: ጥር 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ የተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ በአዲስ አምባ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስጀመሪያ መርሐግብርን አካሂዷል።
በትምህርት ቤቱም 1ሺህ 380 ቅድመ አንደኛ እና አንደኛ ክፍል ተማሪዎች የምገባ ተጠቃሚዎች እንደሚኾኑ ጠቁመዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሙሉ ዓለም አቤ (ዶ.ር) በከተማዋ በ24 ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ መጀመሩን ተናግረዋል።
ለተማሪዎች ምገባ ዝግጅት ከ68 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጓል ያሉት ኀላፊው ዓመቱን ሙሉ ለመመገብም 132 ሚሊዮን ብር ዕቅድ መያዙን ነው የተናገሩት።
25 ሚሊዮን ብር በመንግሥት የሚሸፍን ነው፤ ቀሪው ከረጅ ድርጅቶች እና ከማኅበረሰቡ የሚጠበቅ ነው ብለዋል። የተስተካከለ ብቁ አዕምሮ ያለው፣ ጤናማ፣ ተመራማሪ እና አዋቂ ዜጋን ለማፍራት ምገባ ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በባለፈው ዓመት መንግሥት ከረጅ ድርጅቶች ጋር በመኾን 9ሺህ ለሚኾኑ ተማሪዎች የምገባ መርሐግብር ማካሄዱን አስታውሰዋል።
በዚህ ዓመት የምገባ ሥርዓቱን የበለጠ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል። ምገባ የተማሪዎች የትምህርት አቀባበል ከፍ እንዲል፣ ትምህርታቸውን ተረጋግተው እንዲማሩ እና እንዲከታተሉ ማድረጉን አስረድተዋል።
የተገኘውን ለውጥ መሠረት በማድረግ በዚህ ዓመት ከ20ሺህ በላይ የሚኾኑ ተማሪዎች የምገባው ተሳታፊ እንዲኾኑ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።
የነገ ሀገር ተረካቢዎችን ለማፍራት እና ጤናማ ትውልድን ለመገንባት ተማሪዎች ላይ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
ሥራው የመንግሥት ብቻ መኾን እንደሌለበት፣ ማንኛውም የማኅበረሰብ ክፍል፣ ረጅ ድርጅቶች እና የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
በቀጣይ አሁን ከሚሠራው ከፍ ባለ ቁጥር ለማሳደግ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
