ዲጂታል የሕዝብ መሠረተ ልማት ምንድን ነው?

27
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ዲጂታል 2030 ስትራቴጂ በይፋ ሲጀመር ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች ውስጥ የመጀመሪያው ዲጂታል የሕዝብ መሠረተ ልማት መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በእሳት ዳር ወግ ላይ በነበራቸው ቆይታ ተናግረው ነበር፡፡
ዲጂታል የሕዝብ መሠረተ ልማት የዲጂታል ሽግግርን ለማረጋገጥ ፍትሐዊ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር ይረዳል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮገራም ዲጂታል የሕዝብ መሠረተ ልማት ዘመናዊ የማኅበረሰብ ሥርዓት ለመፍጠር የጀርባ አጥንት በመኾን የሚያገለግሉ መሠረታዊ የዲጂታል ሥርዓቶች መስተጋብር መኾኑን ያስረዳል።
ዲጂታል የሕዝብ መሠረተ ልማት በሰዎች፣ በንግድ ተቋማት እና በመንግሥት መካከል አስተማማኝ እና ቅልጥፍና ያለው የአገልግሎት ግንኙነት እንዲኖርም የሚያስችል ነው።
ጠንካራ ዲጂታል የሕዝብ መሠረተ ልማት ያላቸው ሀገራት የዜጎችን ማንነት በዲጂታል መንገድ በማረጋገጥ፣ ክፍያዎችን በማቀላጠፍ እና የመረጃ ልውውጥን ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ በማከናወን ረገድ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ካፒታል ፈንድ ያስረዳል፡፡
የዲጂታል የሕዝብ መሠረተ ልማት የመንግሥት አገልግሎቶችን በማሳለጥ ረገድ ቁልፍ ሚናን ያበረክታል፡፡ ለዚህ ስኬታማነት ደግሞ ዲጂታል መታወቂያ፣ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የመረጃ ልውውጥ ወሳኝ ናቸው፡፡
ዲጂታል መታወቂያ ዜጎች ማንነታቸውን በቀላሉ አረጋግጠው የባንክ ሂሳብ እንዲከፍቱ እና አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል። የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ገንዘብን በቅልጥፍና እና በአነስተኛ ወጪ ለማስተላለፍም ይረዳል።
በተጨማሪም በተለያዩ ተቋማት መካከል መረጃዎች ደኅንነታቸው ተጠብቆ ለመለዋወጥ የሚያስችል የደኅንነት ሥርዓትም እንዲሁ ወሳኝ ነገር ነው፡፡
ኢትዮጵያም በዘርፉ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታዋን እያፋጠነች ትገኛለች። ለዚህም የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ፣ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና ቴሌብር ተጠቃሾች ናቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleከተማዋ ጽዱ እንድትኾን በተደራጀ መንገድ የጽዳት እና ውበት ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይን ተቀበሉ።