የምንፈልገው ሰላም የእኛን ፍላጎት ብቻ ሳይኾን የሀገርን እና የወገንን ሰላም የሚያሟላ ሊኾን ይገባል።

17

 

ባሕርዳር ፡ ታኅሣሥ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላም የሁሉ ነገር ዋስትና ነው፡፡ ሠርቶ የመለወጥ፣ ወልዶ የማሳደግ፣ ወጥቶ የመግባት በሰው ልጆች የእለት ከእለት ተግባር ውስጥ ከምንተነፍሰው አየር ያልተናነሰ ዋጋ አለው፡፡

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን ይህ አስፈላጊ ሰላም በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች በተለይም ደግሞ በአማራ ክልል ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፤ ማኅበረሰቡም ሰላምን ናፍቋል።

ለአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እና የባሕር ዳርና የሰሜን ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም በሰጡት አባታዊ ምክር እያንዳንዱ ሰው የሰላምን ጥቅም እና ዋጋ ማወቅ ከቻለ ሰላም እንደሚመሠረት ተናግረዋል። ሰላም ከህሊና ሊመነጭ የሚገባው ጉዳይ መኾኑንም አንስተዋል።

ትልቁ ፈተና ግን ሁሉም የየራሱን ፍላጎት መሠረት አድርጎ በእኔ ፍላጎት እና ሀሳብ ብቻ ሰላም ይሁን የሚል እሳቤ ነው ብለዋል። ይህ ደግሞ ሰላምን ማምጣት እንደማያስችል ነው የገለጹት። ሰላምን ለመፍጠር የእኔ ከሚለው ይልቅ የእኛ ከሚለው እሳቤ መነሳት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ጦርነት ያለምንም ጥርጥር አይጠቅምም ያሉት ብጹዕ አቡነ አብርሃም ጎጅ እና ብዙ ነገር እንደሚያሳጣ ተናግረዋል። አይደለም ለሰው ልጆች ለእንስሳት፣ ለአዕዋፋት፣ ለአራዊት እና ለእጽዋት የማይመች መኾኑን ገልጸዋል።

ጦርነት እስካለ ድረስ እረፍት የለም ነው ያሉት። ጦርነት ካለ ውድመት፣ ውድ የኾነው እና መተኪያ የሌለው የሰው ልጅ ሕይወት መጥፋት፣ የሀብት ጥፋት አለ ብለዋል።

ለሰው ልጆች የሚጠቅመው አብሮ መኖር፣ መሥራት፣ ማደግ፣ ችግርን በውይይት መፍታት ነው፤ ቤተ ክርስቲያንም ሁልጊዜ ይህን ታውጃለች ነው ያሉት። ተልዕኮዋም ይህ ነው፤ ከዚህ ውጭ ሰላምን ወደ ሚያሰፍነው ወደ እግዚአብሔር እንደምትጸልይ ተናግረዋል።

የምንፈልገው ሰላም የእኛን ፍላጎት የሚያሟላ ብቻ ሳይኾን የሀገርን ሰላም የሚያሟላ፣ የወገንን ፍላጎት የሚያሟላ፣ የግል ሳይኾን የጋራ እድገትን የሚያመጣ፣ የጋራ ምኞትን የሚያመጣ ፍላጎት ካለ ሰላም ቅርብ ነው ብለዋል።

ፍጥረት በሙሉ ሰላምን የሚፈልግ ነው፤ ከእግዚአብሔር በመለየቷ ሰላምን የተጠማችው ምድር የሰላም ዝናምን ስታገኝ በልምላሜ ታጌጣለች፤ ስለዚህ ምድር ሰላም እንድታገኝ ወደ እግዚአብሔር መጸለይ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

አባቶቻችን ነብያት፣ ቅዱሳን እና ጻድቃን፣ የእግዚአብሔር ባለሟሎች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ወደ እግዚአብሔር ‘ሰላምህን ስጠን’ ብለው መጠየቃቸውንም ጠቅሰዋል።

እግዚአብሔርም በገባላቸው ቃልኪዳን መሠረት ከሦሥቱ አካላት አንዱ ወልድ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በአባቱ እና በራሱ ፈቃድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሰላም ያጣችዋን ምድር ሰላምን ሰጥቷታል ነው ያሉት።

ለምድር የተሰጣት ሰላም ቀላል አይደለም፤ ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል፤ ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እስከ እርገቱ ያለው እውነት ሲቃኝ በልደቱ ሰላምን ሰጠን በልደቱ የሰጠን ሰላም አልበቃ ብሎ ለሰላም መከራን ተቀብሎልንና እስከሞት ድረስ ዋጋ ከፍሎልናል ብለዋል።

የደም ዋጋ የተከፈለበት ሰላም ነው ለሰው ልጆች የተሰጠ፤ የሰው ልጅ ሁሉ ሰላምን አጥብቀው መፈለግ እና መያዝ እንደሚገባ አባታዊ ምክራቸውን ሰጥተዋል። ቤተ ክርስቲያንም ሥራዋ ይህ ስለኾነ አጥብቃ ትመክራለች ነው ያሉት።

ከአላስፈላጊ እልህ፣ እኔ አሸንፍ፣ እኔ አሸንፍ ከሚል አባዜ፣ ብዙ ዋጋ ከሚያስከፍል ነገር በሰላማዊ መንገድ ችግርን መፍታት ይገባልም ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶች ብዙ ስንወቀስ እንሰማለን ያሉት ብፁዕ አቡነ አብርሃም የሃይማኖት አባቶች ግን በሰላም ኑሩ የቤተ ክርስቲያን አስተምሮ እንደሚሰብኩ ገልጸዋል። ተዋጉ የሚል የሃይማኖት አባት ካለ የሃይማኖት ልብስ የለበሰ እንጅ የሃይማኖት ሰው ነው ልንል አንችልም ብለዋል።

ከእኛ ይልቅ ለምድሪቱ ሰላም ይሁን ብሎ ክርስቶስ ለሰላም አውጆልናል ብለዋል። አዋጁን ግን ተቀባይ እና ተጠቃሚ መኾን ይገባል ነው ያሉት። እያንዳንዳችን የየድርሻችን ተግባር ወስደን ለሰላም እጆቻችን የተዘረጉ ይሁኑ በማለት አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።

እምንናገረው ንግግራችንም ሰላምን የሚያበስር፣ ሰላማያዊ የኾነ፣ የጨከነውን እና የጠነከረውን ልብ የሚያራራ ሊኾን ይገባል ነው ያሉት። በጦርነት ምን አገኘን፣ የሰው ልጅ ደም ሲፈስስ ለህሊና እረፍት ይሰጣል ወይ፣ ሰዎች ከቀየ እና ከመንደራቸው ተፈናቅለው አላስፈላጊ በኾኑ የመከራ መንገዶች ሲንገላቱ ማየት ሰው ለኾነ ሁሉ ይቻላል ወይ ብሎ ማሰብ ይገባል ብለዋል።

ነገረን ሰብሰብ አድርጎ እና ጦርነት አይጠቅምም ብሎ መፍትሔውን አፈላልጎ ተወያይቶ ችግርን መፍታት ሰላምን እንደሚያመጣ ተናግረዋል።

ከሁሉም በላይ ፈጣሪን ሰላምህን ስጠን፣ ሰላምን አብዛልን፣ ለሰው ልጆች እና ለዓለም ሰላምን ስጥ ብሎ መጸለይ ያስፈልጋል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የቱሉ አራራ የተቀናጀ ሞዴል መንደርን መረቁ።
Next articleአስታዋሽ ስላለን ደስ ብሎናል።