
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በላሊበላ እየተከበረ ነው፡፡
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሽ መንደር በቤተልሔም የተወለደ የትህትና አምላክ ነው ብለዋል።
እርሱ በተወለደበት በዚያ ዘመን የሮማው ንጉሥ ሕዝብ ያስቆጥር ነበር፤ ትንሿ መንደር ቤተልሔምም በሰው ተመልታ ነበር፤ በዚህም ጊዜ ቅድስት ድንግል ማርያም የነገሥታትን ንጉሥ፣ የጌቶችን ጌታ ወለደችው ነው ያሉት።
በእርሱ መወለድ የ5 ሺህ 500 ዓለም ታሪክ መቀየሩን ተናግረዋል፤ በልደቱ የሰው ልጆች ታሪክም ተለውጧል ነው ያሉት፡፡ በእርሱ መወለድ ሰው እና መላእክት በአንድነት ዘምረዋል፣ በቅዱስ ላሊበላ የሚዘመረው የቤዛ ኩሉ ዓለም ሥርዓትም የሰው እና የመላእክት ዝማሬ ምሳሌ መኾኑን ተናግረዋል።
ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመወለዱ የባርነት ቀንበርን ሰብሮልናል ብለዋል። ኢትዮጵያ የልደትን በዓል በታላቅ ድምቀት እንደምታከብረውም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ለሺህ ዘመናት ሲያከብሩት መኖራቸውንም ገልጸዋል።
በእርሱ መወለድ ፍቅር፣ ሰላም፣ ደስታ እና አንድነት ተሰጥቶናል ነው ያሉት፡፡ በእርሱ መወለድ አዲስ ተስፋ መምጣቱንም ተናግረዋል።
ዓለም አንድነትን፣ ፍቅርን እና ሰላምን ትፈልጋለች ያሉት ብፁዕነታቸው በአንድነት እንነሳ፣ አምላካችን በልደቱ ያደረገውን ነገር እንከተል፤ እርሱ ወደ ምድር የመጣው እኛን ለማዳን ነውና ብለዋል። የሚሻለን በአንድነት መነሳት፣ ፍቅር፣ ሰላም እና ሌሎችን መውደድ ነው።
እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነው፤ እኛም የሰላም አምባሳደሮች መኾን ይገባናል ብለዋል፡፡ ለሰላም፣ ለአንድነት እና ለፍቅር እንነሳ ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
