
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በላሊበላ በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ለመላው የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ ብለዋል፡፡
የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ አዲስ ዘመን እንድናገኝ፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን እንድንሸጋገር ያደረገ፤ ይቅርታ እና እርቅ እንድናገኝ መሠረት የኾንን ነው ብለዋል።
የሰው ዘር ዋጋ ያገኘው በክርስቶስ መወለድ ምክንያት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በክርስቶስ መወለድ አዲስ ተስፋን እና ሕይወትን እንድናገኝ አድርጎናል ነው ያሉት፡፡ የልደት በዓል በኢትዮጵያ በድምቀት እንደሚከበርም ተናግረዋል። የልደት በዓል በታላቀ ድምቀት ከሚከበርባቸው ቦታዎች መካከል እንዱ እና ቀዳሚው ቅዱስ ላሊበላ መኾኑን ገልጸዋል።
በበዓሉ ብዙ ምዕመናን ወደ ስፍራው እንደሚያቀኑ ተናግረዋል። ይህ የኾነው ደግም አባቶቻችን መልካም ሥራ ሠርተው ስላለፉ ነው ብለዋል፡፡ በአባቶቻችን ታሪክ መኩራት ይገባናል ያሉት አፈ ጉባኤዋ የአባቶቻችን ታሪክ መዘከር፣ የእነርሱን ፈለግ በመከተል ላሊበላን መጠበቅ፣ ሰላምን ማጽናት እና ለቱሪዝም የተመቸ ማድረግ ይጠበቃል ነው ያሉት።
የአባቶቻችን ታሪክ መድገም፣ የአባቶቻችን ታረክ መጠበቅ አለብን ብለዋል፡፡ በመተባበር እና በመደጋገፍ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የላሊበላ እና አካባቢው ነዋሪዎች ቅርሱን መጠበቅ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡
የክርስቶስ ልደት አዲስ ተስፋን እንደገለጠልን ሁሉ እኛም የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በልማት ሥራዎች በንቃት መሳተፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ዛሬ ጠንክሮ በመሥራት የሕዝብን ተስፋ ማለምለም እንደሚገባ አመላክተዋል። በክልሉ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ሁለንተናዊ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
እርስ በእርስ ሊከፋፈሉ የሚፈልጉ ኃይሎችን እኩይ ሴራ በማክሸፍ የሕዝብን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ከሁሉም የሚጠበቅ ነው ብለዋል፡፡ የለውጥ ብርሃን መፈንጠቅ መጀመሩን እና ከችግር መሻገራችን አይቀሬ መኾኑን አምነን መሥራት አለብን ነው ያሉት። ጉዟችን ውጣ ውረድ የበዛበት ቢኾንም ፈተናዎችን የምናሸንፍበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ብለዋል።
ከተባበርን የማንሻገረው ችግር የለም ነው ያሉት፡፡ እሴትን፣ ባሕልን፣ ታሪክን እና ሃይማኖትን በመጠቀም የኢትዮጵያን ትንሣኤ ማረጋገጥ እንደሚገባም አፈ ጉባዔዋ ተናግረዋል፡፡ እርስ በእርስ መተማመን እና መደጋገፍ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡
በዓሉ የሰላም እንዲኾንም ተመኝተዋል፡፡
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
