
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የልደት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከሀጥያት ለማዳን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደበት ቀን የሚዘከርበት ዕለት ነው።
በዓሉ የኢየሱስ ክርስቶስ ትህትና፣ ፍቅር እና ራስን ዝቅ አድርጎ ሌሎችን ከፍ በማድረግ ማክበርን ያስተማረበት እንደኾነም የሃይማኖት አባቶች ያስተምራሉ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ክፍል ኀላፊ ሊቀ ጉባኤ ሳሙኤል እንየው ስለ ሊቃውንት አባቶቻችን ‘ምን አይነት ትህትና ነው’ እያሉ ያደነቁት የኢየሱስ ክርስቶስ ትህትና የበዛ እና ግሩም መኾኑን ያስገነዝበናል ብለዋል። አንክሮ እና አድናቆት እንጂ መለኪያም እንደሌለው ተናግረዋል።
አባቶቻችን እግዚአብሔር አምላካችን ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል ይላሉ። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰው ተወልዶ፤ የሰውን ሥጋ ለብሶ እና የሰውን ባህሪ ወስዶ የሰውን ልጅ ከወደቀበት ያነሳበት መንገድ በርካታ ድኅነቶች የተገኙበት መኾኑን አንስተዋል።
አዳም ከበደለ ጀምሮ ክርስቶስ እስኪወለድ ድረስ ለ5 ሺህ 500 ዘመን ድረስ በጥላቻ ግድግዳ የኖሩት ሰው እና መላዕክት ሰው እና እግዚአብሔር በክርስቶስ መወለድ መታረቃቸውን ጠቅሰዋል።
እንስሳት፣ አራዊት እና ሰዎች ኢየሱስ ሲወለድ ‘ዛሬ የዓለም መድኃኒት ተወልዷል’ በማለት ደስታቸውን መግለጻቸውንም ጠቅሰዋል። በዚህም ጥላቻ ፈርሶ ፍቅር መገንባቱን ገልጸዋል።
የክርስቶስን ልደት ስናከብር ልዩነታችንን አጥብበን፣ የተጣላን ታርቀን በአንድነት እና በኅብረት መኾን አለበትም ነው ያሉት።
በልዩነት፣ በጥላቻ እና በተንኮል ውስጥ ኾነን የምናከብረው የኢየሱስ ክርስቶስ በዓል ግን ሥጋ መብላት ብቻ ይኾናል ብለዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለሙ ሁሉ በእጁ፤ ሁሉ በደጁ ኾኖ ሳለ የሰውን ልጅ ለማዳን ሲወለድ እና በምድር ላይ ተመላልሶ ሲያስተምር የተገበራቸው ድርጊቶች ሁሉ ለማስተማር ሲል መኾኑን ጠቅሰዋል።
አምላክ ኾኖ ሳለ ስጋ ለብሶ ከሰው መወለዱ፣ በድሃ መንደር በከብቶች በረት መወለዱ፣ ከላሞች እስትንፋስ ሙቀት ማግኘቱ የትህትናው አስተምህሮ መገለጫዎች መኾናቸውን ጠቅሰዋል።
የሰው ልጅም በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እና ትህትና ሊማራቸው ከሚገባው ሥርዓቶች ውስጥ አንዱ ራስን ዝቅ አድርጎ ሌሎችን በማክበር፣ በመተሳሰብ እና በመረዳዳት መኖርን ነው ብለዋል።
ክርስቶስን እመስላለሁ፤ የክርስቶስ ልጅ ነኝ፤ ክርስቶስን አመልካለሁ የሚል ሁሉ ትህትናን ማድረግ ይጠበቅበታል።
ራስን ከማስቀደም ታቅቦ ለሌሎች ዕድል መስጠት እና ለወንድሙ በማሰብ የክርስቶስ ተከታይ መኾኑን ማረጋገጥ እንዳለባቸውም መክረዋል።
ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስን በዓል ሲያከብሩ የክርስቶስን ትህትና መመስከር ብቻ ሳይኾን መተግበርም እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል። ይህንን ካላደረግን ሁሉም ከንቱ ነው ብለዋል።
ራስን ማስቀደም እና ሰዎችን ዝቅ አድርጎ በማየት ማዋረድ በአሁኑ ዘመን የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው። ነገር ግን እኔ ከማለት ወጥቶ ሌሎችን ማሰብ፣ የተናቁትን ማቅረብ፣ ክርስቶሳዊ መኾን እንደሚገባም ተናግረዋል።
ራሱን ያስቀደመ ዲያብሎስ ብቻ ነው ያሉት ሊቀ ጉባኤ ሳሙኤል የምንፈልገውን የምናገኘው ሰዎችን ስናከብር፣ በትህትና ስንጓዝ እና ራሳችን ዝቅ ስናደርግ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
