የገና ጨዋታ የእኩልነት መገለጫ ነው።

27

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የገና ጨዋታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ጋር የመጣ ሥነ ሥርዓት እንደኾነ ይነገራል። ጨዋታው አዝመራ ከተሠበሠበበት ታኅሣሥ ወር ጀምሮ የሚከወን ነው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የምሥራቀ ፀሐይ ደብረ ማርያም ገዳም የመጻሕፍት መምህር የኽይስ የሻምበል የገና ጨዋታ የኢትዮጵያ ባሕላዊ ትውፊት ነው ብለዋል።

ጨዋታውን ለማከናዎን የግድ ሁለት ቡድኖች ያስፈልጋሉ የሚሉት መምህሩ ቡድኖቹ በጎጥ ወይም ቀበሌ አልያም በሰፈር ይዋቀራሉ ነው ያሉት።

በቡድኖቹ የሚካተቱት ተጫዋቾች በአቅም፣ በፍጥነት፣ በቅልጥፍና በጥበብ፣ በዕድሜ አቻ እንዲኾን በሚል ሁለት በሽምግልና ወይም በነገር አዋቂነት ስመ ጥር የኾኑ አባቶች በቡድን አባትነት ይሰየማሉ ብለዋል።

በቡድን አባትነት የተሰየሙት አባቶችም ሁሉም ሰው መቧደኑን ካረጋገጡ በኋላ ጨዋታውን ያስሄዳሉ።

የገና ጨዋታ የሁሉም ኀብረተሰብ ጨዋታ ነው የሚሉት መምህሩ በገና ጨዋታ ሎሌው ከጌታው ያለምንም ሃፍረት እና እፍረት ይጫወታል፤ ሎሌው ጌታውን በጨዋታ ሂደት ድንገት ቢጎዳ ጌታው አይቆጣም። ቂም ቁርሾ አይኖርም ነው ያሉት።

“በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ፤ በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” መባሉም ለዚህ ነው ብለዋል መምህር የኽይስ።

የገና ጨዋታ አሸናፊው ቡድን ተሸናፊውን በግጥም፣ በስንኝ እና በሽለላ ይነቅፋል ብለዋል። ሀሳብ እንጅ ሰውነት አይነቀፍም የሚሉት መምህሩ ከጨዋታው በኋላ ተይዞ የሚያድር ቂም እና በቀል እንደማይኖር ተናግረዋል።

በገና ጨዋታ ወቅት የተነቀፈው ቡድን የንጉሥ ልጅ ያለበት ቢኾን እንኳ ቂም አይዝም ነው ያሉት። በመጨረሻም ሁሉም ተሳስሞ፣ አብሮ በልቶ እና ጠጥቶ ይለያያል ያሉት መምህሩ ይህም ጨዋታው ምን ያህል የነጻነት መገለጫ መኾኑን ያሳያል።

የገና ባሕላዊ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቀደም ባለው ጊዜ የምታደርጋቸው ክዋኔዎች ምን ያህል፣ መቻቻልን፣ መከባበርን፣ ብዝኃነትን እና ትዕግስትን የተላበሱ እንደነበሩ ያመላክታል። በቃ የገና ጨዋታ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ነው ብሎ መግጽ ይቻላል ብለዋል።

የቀደመው ትውልድ ከገና ጨዋታ የመቻቻልን እና የትዕግስትን አስተምህሮ አቀብሎን ነው ያለፈው የሚሉት መምህሩ ይህ ትውልድም የቆየውን የገና ባሕላዊ የጨዋታ ትውፊት አጥብቆ በመያዝ ለቀጣዩ ትውልድ ማሻገር ይገባዋል ነው ያሉት።

መሰል ትውፊቶች ሀገር እና ኀብረተሰብ የማነጽ እና የመገንባት አቅማቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪው አባ ታምራት ደስታ በእነርሱ ጊዜ የገና ጨዋታ መቻቻል የሰፈነበት እንደነበር ነግረውናል።

ይህ ትውልድም እንደ ገና ያሉ የተቧድኖ ባሕላዊ ጨዋታዎችን ከጨዋታ ባለፈ በወል አስተሳሰብ እና ኀብረት ለሀገር ክብር ማዋል ይኖርበታል ነው ያሉት።

የቅንባባ ነዋሪው አያሌው ሞኝነት የገና ጨዋታ ለእርስ በእርስ ትውውቅ እና መግባባት ፋይዳው ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ጨዋታው እየተቀዛቀዘ መምጣቱን ነው የጠቆሙት።

በሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleድጋፉ ባይደረግልን ኖሮ ጾም ሳንፈታ እንውል ነበር።
Next articleየኢየሱስ ክርስቶስን ልደት የሚያከብር ሁሉ ትህትናን ያድርግ።