የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ሲከበር የተቸገሩትን በማሰብ ሊኾን እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች አሳሰቡ።

29
አዲስ አበባ፡ ታኅሣሥ 28/2018 (አሚኮ) በኢትዮጵያ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ይከበራል።
የ2018 ዓ.ም የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አስመልክቶም የሃይማኖት መሪዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሃይማኖት አባቶቹ በመልዕክታቸው አማኞች የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ሲያከብሩ እና ሲያስቡ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣበትን ምስጢር በመረዳት እና በመገንዘብ ሊኾን ይገባል ብለዋል።
የሃይማኖት አባቶቹ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ሁሉ የልደት በዓልን በተለያዩ ዝግጅቶች ሲያሳልፉ የተቸገሩትን በማሰብ ሊኾን እንደሚገባም አሳስበዋል።
ስለሰው ልጆች ሀጢያት ወደ ምድር የመጣውን የኢየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮ ተግባራዊ በማድረግ ሁሉም በፍቅር እና በሰላም ሊኖር እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዓሉ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ጥልቅ ፍቅር በተግባር የገለጸበት ነው ብለዋል።
የሃይማኖቱ ተከታዮችም የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ሲያከብሩ ለፈጣሪ ጸሎት እና ምሥጋና ከማቅረብ ባሻገር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት እና በመተሳሰብ ሊኾን እንደሚገባ አሳስበዋል።
በዚህም በተለያየ ምክንያት የምግብ፣ የልብስ እና መጠለያ እጥረት የገጠማቸውን ወገኖች በማገዝ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ መደገፍ እና ማገዝ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ የኢየሱሰ ክርስቶስ ልደት ሲከበር አቅመ ደካማና ረዳት የሌላቸውን ወገኖች በማሰብ ሊኾን እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተለይም በዓሉ ሲከበር ሕሙማንን በመጠየቅ፣ አቅመ ደካማ፣ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን ወገኖች ካለን በማከፈል እና የታረዙትን በማልበስ ማሳለፍ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ጸሐፊ ቄስ ደረጄ ጀምበሩ በኢትዮጵያ እና በተለያዩ ሀገራት ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የ2018 ዓ.ም የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል የደስታ እና የፍቅር እንዲኾን ተመኝተዋል፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ የእግዚአብሔርን ይቅር ባይነት እና ለሰው ልጆች ያለውን ታላቅ ፍቅር የሚያሳይ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ልዩነቶችን በእርቅ በመፍታት ለዘላቂ ሰላም መትጋት ይገባል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ራሔል ደምሰው
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር 381 ቤቶችን ከሙሉ የቤት ዕቃና ከበዓል ማሳለፊያ ጋር በስጦታ አስረከበ።
Next articleየሰላምን መንገድ መምረጥ አዋጭ ነው።