የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ሰው ከእግዚአብሔር እና ከመላዕክት ጋር የታረቀበት ነው።

18
ባሕርዳር፡ ታኅሣሥ 28/2018ዓ.ም (አሚኮ) በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል ታኅሣሥ 29 ቀን የሚከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አንዱ ነው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እና የባሕር ዳር እንዲሁም የሰሜን ጎጃም ሀገረስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም “የአምላካችን እና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ ድንገተኛ አይደለም፤ በአበው ትምህርት እና በነቢያት ትንቢት አስቀድሞ የተነገረ እና የተረጋገጠ ነው ብለዋል።
በቃልኪዳኑ መሠረት ቃልኪዳኑንም ሊፈጽም ከቅድስተ ቅዱሳን ከድንግል ማርያም ተወልዷል፤ ወደ ዚህ ዓለምም መጥቷል ነው ያሉት።
ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት አካባቢ የሚገኙ ሰዎች በቅርብ ኹነው ፈልገው ለማግኘት ሳይሞክሩ በሩቅ ያሉ እና ባይዳን የተባሉ፤ ከሩቅ ምሥራቅ ተነስተው የተወለደው የአይሑድ ንጉስ ከወዴት አለ እያሉ ሰብዓ ሰገል (የጥበብ ሰዎች) ፍለጋ እንዳደረጉ እና በኮከብ ተመርተው ኢየሱስ ወደ ተወለደባት ቤተልሔም እንደተጓዙ በቅዱስ መጽሐፍ መነገሩንም ጠቅሰዋል።
ንጉሱ በቤተ መንግሥት እና በባለጸጎች ቤት ሳይኾን በከብቶች በረት ተወልዶ እንስሳቱ በእስትንፋሳቸው እዳሞቁትም ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚናገር አስረድተዋል።
የሰማይም የምድሩም ንጉሥ ራሱን ችግረኛ አድርጎ በበረት መወለዱ ለሰው ልጆችም አስተማሪ እና ቸርነቱን እንድናደንቅ የሚጋብዝ እንደኾነም ጠቁመዋል።
“የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ሰው ከእግዚአብሔር እና ከመላዕክት ጋር የታረቁበት ነው” ብለዋል።
ዛሬ ላይ በዓለ ልደቱን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልጆች ሲያከብሩ እንደ ሰብዓሰገል ሰዎች ሁልጊዜም ፍለጋቸው ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ እንዲኾን እና በዚህም ክብርን ሊያገኙ ይገባል ብለዋል።
የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የደስታ እና የፍቅር ዕለት እንደኾነም አስገንዝበዋል። ብፁዕ አቡነ አብርሃም የፍቅር እና የደስታ በዓልነቱ ግን በመጠጥ ብዛት፣ በጥላቻ፣ የማያስፈልጉ የነውር ሥራዎችን በመሥራት እና ሰውን በማሳዘን እንዳልኾነም ጠቁመዋል።
የሃይማኖቱ ተከታዮች በዓሉን ሲያከብሩ የቅድስት ቤተክርስቲያን አስተምሮ የኾኑ ተግባራትን ማለትም የተቸገሩትን በማሰብ እና በመርዳት፣ የታሰሩትን በመጎብኘት፣ የታመሙትን በመጠየቅ፣ ያዘኑትን በማጽናናት፣ በልዩ ልዩ ፈተና ውስጥ የሚገኙትን በማበረታታት እና የተጣሉትን በማስታረቅ እንዲኾንም አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል።
የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ሰው እና መላዕክት በአንድነት የዘመሩበት፣ ለምድር ሰላም ተብሎ የታወጀበት፣ ሰላም የተነገረበት ልዩ በዓል መኾኑንም ገልጸዋል።
የአምላክ መወለድ የሁሉም ሰላም በመኾኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንዲሰጠን እንለምነው፣ እንጠይቀው እንዲሁም ለሰላም ሳንገፋፋ በጋራ እንሥራ በማለት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የጤና፣ የሕይወት፣ የበረከት፣ የመረዳዳት፣ የፍጹም ደስታ እንዲኾንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የልደት በዓል ጨለማ በብርሃን፤ ሞት በሕይወት የተሸነፈበት የድል ቀን ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ማዕድ አጋሩ።