
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አሥተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም እኛ በሕይወት እንኖር ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ዓለም የላከ እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለ2018ዓ.ም በዓለ ልደቱ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ ነው ያሉት።
የእግዚአብሔር ፍቅሩ በእኛ ዘንድ ተገለጠ፤ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነው ብለዋል። በዓለ ልደት የእግዚአብሔር ሰላምና ፍቅር ለሰው ልጆች ሁሉ የታወጀበት ዕለት መኾኑን ገልጸዋል።
እግዚአብሔር ሰብዓዊነትን በምልአት ተዋሕዶ በዓለም እንዲገለጥ የሆነበት ዋና ምክንያት በሕይወት እንድንኖር ነው፤ ይህንንም ያደረገው ከሁሉ በላይ የኾነ ሌላ ገፊ ኃይል ገፋፍቶት ሳይኾን ድንበር የለሽና ፍጹም ፍቅሩ አነሣሥቶት ነው ብለዋል።
የእግዚአብሔር ፍቅር እኛ ከምናውቀው ፍቅር ሁሉ በላይ ነው፤ ለፍቅርና ሰላም ሲል እስከ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚዘልቅ ፍቅር ሰጥቷል ነው ያሉት።
እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፈቃድ እኛ በሕይወት በሰላምና በፍቅር እንድንኖርለት ከኾነ የእኛ ግብረ መልስም ከዚህ የተለየ ሊኾን አይገባም ነው ያሉት። እግዚአብሔር ጠላቶቹን ለማዳን እንጂ ለማጥፋት አልመጣም፤ የእኛም ሕይወት የሚጠበቀው አንዱ ሌላውን በማዳን እንጂ በማጥፋት እንዳልኾነ ጌታችን በቃልም በተግባርም በአጽንዖት ነግሮናል ብለዋል።
በዚህ አስተሳሰብና እምነት እንድንኖርም አዞናል ነው ያሉት። በቃሉ ለመኖርና ለእሱ ለመታዘዝ ቃል የገባን እኛ ክርስቲያኖች ይህን ሁሉ እርግፍ አድርገን በመተው እርስ በእርስ ለመጠፋፋት መሽቀዳደም ምን ይሉታል? ይህስ ለማን ይበጃል? ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
የአንድ ሀገር ሕዝቦች ይመካከራሉ፣ ይቻቻላሉ፣ ይታገሣሉ፣ ጊዜ ሰጥተው ያስቡና መፍትሔ ያበጃሉ እንጂ ማን በማን ላይ ይነሣል? ይህ ለማንኛችንም አይበጀንምና ወደ አዕምሮአችን እንመለስ የሚል ጥሪ የወቅቱ የቤተ ክርስቲያናችን መልእክት ነው ብለዋል።
ይህንን የተቀደሰ በዓል ስለ ሀገራችን ዘላቂ ሰላም በመጸለይ፣ በማሰብ እና በልዩ ልዩ ምክንያት የምግብ፣ የልብስና የመጠለያ እጥረት ያጋጠማቸው ወገኖቻችንን በመደገፍና በመርዳት ለእግዚአብሔር ክብር ብለን ለሀገር አንድነትና ለሕዝብ ፍጹም ሰላም መስፈን ከልብ በመነሣሣት እንድናከብር አባታዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
