
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአዋሽ ባንክ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ በባሕር ዳር ከተማ ከ200 በላይ ለሚኾኑ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ አደረገ፡፡
ድጋፍ የተደረገላቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ሴቶች፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ናቸው፡፡ ባንኩ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ ለእያንዳንዳቸው አምስት ሊትር የምግብ ዘይት፣ 25 ኪሎ ግራም የስንዴ ዱቄት እና 3 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ ነው ያደረገው፡፡
ግለሰቦቹ በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን እና በዓሉን ከቤተሰቦቻቸው ጋር በፍቅር ሳይጨናነቁ እንደሚያሳልፉ ገልጸዋል፡፡ ለተደረገላቸው ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በድጋፍ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አሥኪያጅ መልዓከ ሰላም ኤፍሬም ሙሉዓለም በዓሉ የሰው ልጅ ከኃጥያት የዳነበት የደስታ መገለጫ በዓል ነው ብለዋል።
በበዓሉ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የአዋሽ ባንክ ድጋፍ ማድረጉ ለወገን ያለውን ክብር ያሳየ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡
ችግረኞችን መርዳት ራስን መርዳት ነው፤ በሰማይም በምድርም ዋጋ ያለው ተግባር መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ድጋፍ ላደረገው አካልም ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የአዋሽ ባንክ ሰሜን ምዕራብ ሪጅን ዋና ዳይሬክተር መሠረት አምበሉ ባንኩ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን ለመወጣት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ እንደ ሀገር ሰው ተኮር የድጋፍ ሥራዎች ማከናወኑን አስታውሰዋል፡፡
በበዓላት ወቅት በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ እንደሚያደርግም አንስተዋል፡፡
ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በክልሉ ከ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ በባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ እንጅባራ እና ደብረ ማርቆስ ከተሞች ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ ከ200 በላይ ወገኖች ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ባንኩ ወደፊትም ድጋፉን በቁጥር እና በተደራሽነት በማስፋት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ አዋሽ ባንክ ያደረገው ድጋፍ ለሌሎች ተቋማትም አስተማሪ ነው ብለዋል፡፡
ለበዓላት ከሚደረገው ድጋፍ በተጨማሪ ለሚሠሩ ሴቶች የብድር ትስስር በመፍጠር እና ለተቸገሩ ወገኖች የጤና አገልግሎት እንዲያየገኙ የጤና መድኅን ሽፋን እገዛ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ባንኩ በዓሉን አስመልክቶ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ያደረገው እገዛ የመረዳዳት ባሕላችን እያደገ መምጣቱን ያሳየ ነው ብለዋል፡፡
ሁሉም ሰው ተመሰሳይ ሁኔታ ላይ አይኖርም፤ በዓል ሲመጣ አቅም የሌላቸው ወገኖች በዓሉን ከፍቷቸው እንዳያሳልፉ መረዳዳት አስፈላጊ ነው፤ የራስን ወገን ራስ መርዳት በጣም ኩራት ነው ብለዋል፡፡
ተረጅነት የማይፈለግ ቢኾንም ማኅበራዊ ክስተት በመኾኑ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ድጋፍ አድራጊ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ያላቸውን በማካፈል በዓሉን በሠላም እንዲያሳልፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
