
ባሕርዳር፡ ታኅሣሥ 27/2018 (አሚኮ) መንግሥት ለዘላቂ ሰላም ግንባታና ችግሮችን በምክክር የመፍታት ባሕል እንዲዳብር በትኩረት እየሠራ መኾኑን የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ገልጸዋል።
መንግሥት ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልንና ውይይትን እንደመርህ በመውሰድ ለሀገር ዘላቂ ብልጽግና በትጋት እየሠራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
መንግሥት ከለውጡ ማግሥት ጀምሮ በሀገር ውስጥ እና በቀጣናው የዘላቂ ሰላም ግንባታ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ መኾኑን ተናግረዋል።
ጠንካራ ሀገር የሚገነባው በሕዝቦች አብሮነት እና በመመካከር እንደኾነ መንግሥት ጽኑ አቋም እንዳለውም ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ስር ሰደው የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እና በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱ የዚሁ ቁርጠኝነት ማሳያ መኾኑን ጠቁመዋል።
የፖለቲካ ፍላጎታቸውን በኃይል ለማሳካት የሚሞክሩ አካላት ከስህተታቸው ተመልሰው ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጡ መንግሥት በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ እያቀረበ እንደኾነም ገልጸዋል።
በዚህም በተለያዩ ክልሎች በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች የመንግሥትን የሠላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ሕይወት በመመለስ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በሕዝቦች መካከል መቀራረብ እንዲኖር፣ የጋራ ትርክት እንዲገነባ እና ሀገር በቀል የችግር መፍቻ ሥርዓቶች እንዲዳብሩ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው ይህም ዜጎች በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ለሰላም ግንባታ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ያለመ እንደኾነ ነው የገለጹት።
ሀገራዊ የብልጽግና እና የዕድገት ጉዞን ለማሳካት ሰላም ወሳኝ መኾኑን የገለጹት ሚኒስትሩ ለዘላቂ ሰላም ግንባታና ለልማት መሳለጥ መንግሥት በትኩረት መሥራቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
