
ባሕርዳር፡ ታኅሣሥ 27/2018 (አሚኮ) የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ የተቀናጀ የቱሪዝም አሥተዳደር ሥርዓት( ITMS) ሥራ የማስጀመሪያ ሥነሥርዓት እያካሄደ ነው።
የተቀናጀ የቱሪዝም አሥተዳደር ሥርዓቱ ( ITMS) የአማራ ክልል ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ከአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖለጅ ቢሮ ጋር በትበብር የለማ ነው።
የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋዬ ክልሉ በቱሪዝም ጉዞው በተበታተነ አኳኋን ተጉዞ ባለው ሃብት እና የመልማት ጸጋ ልክ ሳይጠቀም መቆየቱን ተናግረዋል።
ያለው ሃብት እና ጸጋ ላይ ፈጠራን አክሎ ክልሉን በቱሪዝም ሃብት ማሳደግ እና ተወዳዳሪ እንዲኾን ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ምድር ውብ እና ድንቅ ነው ያሉት ኀላፊው ይህን ድንቅ ምድር በሲስተም ለዓለም ማድረስ እና ዓለም እንዲጎበኘው ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ዛሬ የማስጀመሪያ ሥነሥርዓት እየተከናወነለት የሚገኘው መተግበሪያው የቱሪዝም ጸጋዎችን፣ የቱሪስት መዳረሻዎችን፣ የቱሪዝም ምርት፣ አገልግሎቶች እና አገልግሎት ሰጭዎችን በአንድ ስፍራ የሚያስተዋውቅ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
መተግበሪያው በቱሪዝም እሴት ሰንሰለት ውስጥ የተሠማሩ ቁልፍ የቱሪዝም ተዋንያን በአንድ ስፍራ የሚገናኙበት፣ አገልግሎቶቻቸውን እና ምርቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት፣ የሚሸጡበት እና ከቱሪስቶች ጋር የሚገናኙበት በመኾኑ ለዘርፉ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
