
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አሁን በኅብረት የተሰሙ ድምጾች፣ ሰላምን የተጣሩ አንደበቶች፣ ለሰላም የተዘረጉ እጆች፣ ወደ ሰላም የተጓዙ እግሮች፣ ሰላምን የሻቱ ልቦች በርክተዋል። አሁን ለሰላም የሚዘምሩት በዝተዋል፤ ሰላምን የሚፈልጉት አያሌ ኾነዋል።
ሰላም ጠፍታ ከርማለችና ቀየው ደስታ ርቆታል፤ እልፍኙ ፍስሃ ጎድሎበታል፤ ጎዳናው በሰላም የሚንቀሳቀስ ሕዝብ ናፍቆታል። ሰላም ጠፍታ ከርማለችና የቀየው እረኞች ሜዳውን በጨዋታ አይሞሉም፤ ላሞች እና በሬዎች በግጦሽ አይሰማሩም፤ ሰላም ጠፍታ ከርማለችና በግ እና ፍየሎች፣ ፈረስ እና በቅሎዎች ሳይደነግጡ አይውሉም።

ሰላም ጠፍታ ከርማለችና የተቀደደን ሰማይ የሚሰፉት፣ በዘንጋቸው ደም የሚያደርቁት፣ በልዝብ አንደበታቸው ጥልን የሚጥሉት፤ ቁርሾን የሚያክሙት፣ ቂምን የሚያሽሩት ሽማግሌዎች እንደ ወትሮው አይከበሩም፤ ሰላም ጠፍታ ከርማለችና በአምላክ ስም ገዝተው ወንዝ የሚያቆሙት፤ ለግድያ የሚፈላለጉትን ገስጸው በፍቅር የሚያስተቃቅፉት፣ ለሰላም የሚጸልዩት፣ ለሰላም የሚማጸኑት፣ ሰውን ከሐጥያት ማሳሪያ የሚፈቱት፣ ከአምላክ ዘንድ የከበረ መንፈሳዊ ሥልጣን የተቸሩት የሃይማኖት አባቶች ቃላቸው አይሰማም። ይልቅስ ዝናብ ያፈራቸው ሽማግሌዎች፣ አምላክ መርጦ የሾማቸው የሃይማኖት አባቶች በአደባባይ ተንበርክከዋል፤ ተዋርደዋል፤ ተንገላትተዋል፤ ተገድለዋል እንጂ።

ክፉ ዘመን መካሪ ሽማግሌዎችን፣ ዘካሪ የሃይማኖት አባቶችን ያሳጣል፤ የሚመክሩ ሽማግሌዎች፣ የሚገስጹ የሃይማኖት አባቶች በጠፉ ጊዜ ምድር የመከራ ጽዋን ትቀበላለች፤ አንተም ተው አንተም ተው የሚል ይጠፋና በክፉ ሥራ ትታመሳለች። ተግሳጽን በሚንቁ እጆች ትደማለች።
ሰላም ጠፍታ ከርማለችና ኖረው የሚመርቁት አረጋውያን ሞተዋል፤ አድገው ሀገር የሚረከቡት ሕጻናት ያለ በደላቸው የግፍ ጽዋ ተቀብለዋል፤ ከዕውቀት ብርሃን ተከልክለዋል። ሰላም ጠፍታ ከርማለችና ትምህርት ቤቶች ፈርሰዋል፤ የተማሪ መቀመጫ ወንበሮች ለስጋ መጥበሻ ተቃጥለዋል።
ደጋጎቹ ገበሬዎች እያረሱ እሸት የሚበሉባቸው፤ ገበያውን እያጠገቡ ሀገር የሚቀልቡባቸው በሬዎች ከቀንበራቸው እየተፈቱ ታርደዋል፤ ወተት የሚሰጡ ላሞች ከጥጆቻቸው እየተነጠሉ ተሸልተዋል፤ የሀገሬው ሰው በመንደሩ እና በአድባሩ ለመኖር ሰግቷል።

ሰላም ጠፍታ ከርማለችና ንጹሐን ያለ በደላቸው ሞተዋል፤ ለዓመታት የተሠሩ ልማቶች ፈርሰዋል፤ ታዳጊዎች ተስፋቸውን ተነጥቀዋል፤ እናት እና ልጅ ተለያይተዋል፤ ሰዎች እንደ ፍየል ግልገል እየተሰረቁ ለገበያ ቀርበዋል፤ ገንዘብ እየተጠየቀባቸው ተሽጠዋል፤ አባት እና እናት ለገበያ የቀረቡ ልጆቻቸውን ጋቢ አንጥፈው ለምነው ገዝተዋል፤ ገንዘብ ያላገኙ ወላጆችም ልጆቻቸውን አጥተዋል።
ጎዳናዎች ሰላም አልነበራቸውምና ወገን ከወገኑ እንዳይገናኝ ተከልክሏል፤ ልጆች ከእናት እና አባቶቻቸው ተነጥለው ኖረዋል፤ ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ልጆች መምጫ መንገድ አጥተው በስልክ ቀብረዋል፤ እርም ሳያወጡ በመሪር ሀዘን ቀርተዋል። የሰላም እጦት እልፍ ነገር አሳጥቷል፤ እልፍ ነገር ቀምቷል።
አሁን ግን የሰላም ተስፋ ታይታለች፤ የሰላም ጀንበር በምሥራቅ ንፍቅ ፈገግ ብላለች፤ ግጭት ጥቁር ደመና የጣለባት ቀን መፍካት ጀምራለች።

ከሁለት ዓመታት በላይ የኾነው የአማራ ክልል ግጭት አያሌ ጉዳቶችን አድርሷል። ያ ደግ፣ ኩሩ፣ ጀግና፣ እንግዳ ተቀባይ እና አስታዋይ ሕዝብ የመከራ ቀንበር ተሸክሟል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች እድሜያቸው በከንቱ ባክኗል፤ ያለ እረፍት የሚሠሩ ባለሃብቶች ተሰደዋል፤ ቀን እና ሌሊት ሲሠሩ የነበሩ ፋብሪካዎች ፈተና በዝቶባቸዋል።
ይህን ሁሉ ችሎ የኖረው ሕዝብ አሁን ላይ ትክሻዬ ጎብጧል፤ ትዕግሥቴም አልቋል ብሏል። አሁን የጋለ የመከራ ቀንበር ተሸክሞ የከረመው፤ ከዛሬ ነጋ ይሻላል ብሎ የታገሰው ሕዝብ ግጭትን አውግዟል፤ ለሰላም በአንድነት ተነስቷል፤ ሰላም ይኾን ዘንድ በአንድነት ድምጹን አሰምቷል። በኅብረትም ስለ ሰላም ዘምሯል፤ ግጭትን እና ክፉ ሥራን በአደባባይ ኮንኗል፤ ቀዬው አማን ውሎ አማን ያድር ዘንድ ከልብ ሽቷል፤ ከልብም ተነስቷል።
ከሰሞኑ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ሕዝባዊ ውይይቶች ተደርገዋል። ሕዝብም ከሁለት ዓመታት ለተሻገረ ጊዜ ያሳለፈበትን የፈተና እና የችግር ጊዜ አውጥቶ ተናግሯል። በሰላም እጦት ዋጋ መክፈሉን፣ የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ መኾኑን ገልጿል።
በግጭት ውስጥ ከዕለት እንጀራ እስከ ቋሚ ንብረት ተቀምተናል፤ ሃብት እና ንብረታችንን በግዴታ ሰጥተናል፤ ልጆቻችን ከትምህርት ገበታ ርቀዋል፤ ወገን ከወገኑ በሀዘኑም በደስታውም ጊዜ እንዳይገናኝ ኾኗል፤ መከራው በዝቷል፣ አሁን ግን የትዕግሥትም ልክ አለው፤ የመከራም መቋጫ አለው ይበቃል ብሏል።
ከዚህ በላይ ክፉ ሥራን አንተጋስም፣ ግጭትንም አንሸከምም ነው ያለው። በአማራ ክልል ያለው ግጭት ሕዝብን የሚጎዳ እንጂ የሚጠቅም አይደለም፤ ድርጊቱ እሴት የሚያጠፋ፣ ሀገርን የሚሸጥ ነውና። በሕዝብ ደም መነገድ ይበቃል፤ ከሕዝብ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር አብሮ እየሠሩ፣ ሕዝብን እያሰቃዩ ለሕዝብ እቆረቆራለሁ ማለት ውሽት ብሏል።

የአማራ ክልል ሕዝብ ከዚህ በላይ በመከራ እና በስቃይ ውስጥ መኖር ይበቃዋል፤ ሁሉም ሰላም ላይ መሥራት አለበት፤ በጫካ ያሉትን እየመከርን እናምጣቸው፣
የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለሕዝብ ሲሉ የዕውነት መምከር እና ሰላምን ማረጋገጥ አለባቸው፤ ሰላምን ከሚሰብኩት፣ ለሰላም ከሚጸልዩት በተቃራኒ ከሃይማኖቱ አስተምህሮ ውጭ የሚሠሩ አንዳንድ የሃይማኖት አባቶችም ይታቀቡ ነው ያለው።
የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የሚፈታው በአፈሙዝ ሳይኾን በውይይት እና በምክክር መኾኑም በውይይቶቹ በስፋት ተነስቷል፤ ለሰላም ካልሠራን ሁሉም ነገር አይሳካም፤ የልማት ጥያቄ የሚፈታው ሰላም ሲረጋገጥ ነው፤ ሰላምን ለማረጋገጥ በጋራ እንሥራ፣ አንድነታችንን እናጠንክር፤ ችግሮችን በውይይት መፍታት እንልመድ፤ መገዳደል ይበቃል፤ ሁሉም ልጆችን ይቆጣ፣ ሕዝብን እያዋረደ ያለው ግጭት ሊቆም ይገባል ብሏል።
የውስጥ አንድነትን በማጠናከር የኢትዮጵያን ከፍታ ማረጋገጥ፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ይገባናል፤ ውስጥ ላይ ያለው ግጭት ሀገርን የሚያሳንስ እና ለውጭ ጠላት አሳልፎ የሚሠጥ እንጂ አይጠቅምም ነው ያለው። ሰላም ለሁሉም ታተርፋለች፤ ለሁሉም ትጠቅማለችና ሕዝብ ሰላምን ፍለጋ ተነስቷል፤ ግጭትንም አምርሮ ጠልቷል።
ከወደዳችሁንስ ሰላም ስጡን፤ ካከበራችሁንስ ምክራችንን ስሙን፤ አፈሙዛችሁን አዙሩልን፤ ግጭትን ተውልን፤ ሀገሩን ሰላም አድርጉልን፤ ከወገን ጋር በሀዘን እና በደስታው እንዳንገናኝ አትከልክሉን፤ ሠርተን እንዳንበላ፣ ወልደን ለቁም ነገር እንዳናበቃ አታደርጉን፣ ከተቆረቆራችሁልንስ የጠፋችውን ሰላም መልሱልን ብሏል።
ሕዝብ ለሰላም መነሳቱን፣ በግጭት መሰላቸቱን ያዩ ታጣቂዎችም የሰላም አማራጭን እየመረጡ፤ ከጫካ እየወጡ ወደ ቤት እየመጡ ነው። ሰላም የሚመርጡ ሁልጊዜም ጀግኖች እና አትራፊዎች ናቸው። ሕዝብ ይወዳቸዋል። በፍቅርም ይቀበላቸዋል። በፍቅርም እየተቀበላቸው፣ ምክሩንም ስለሰሙ እያመሠገናቸው ነው።
ሰላም ሲኖር ጎዳናዎች የናፈቁትን ሕዝብ ያገኛሉ፤ ሰላም ሲኖር ትምህርት ቤቶች ይከፈታሉ፤ ሕጻናት ይማራሉ፤ ነጋዴዎች ይነግዳሉ፤ ገበሬዎች ያርሳሉ፤ አረጋውያን በዕድሜ ይሰነብታሉ፤ ሕጻናት በሞገስ ያድጋሉ፤ የተዘሩት ይበቅላሉ፤ የበቀሉት ያድጋሉ፤ ያደጉት ያብባሉ፤ ያበቡት ያፈራሉ። ሰላም ከሁሉም ትልቃለች። ሰላም ሁሉንም ትሰጣለች።
ሁልጊዜም ለሰላም በአንድነት ተነሱ፤ የሰላምን ጎዳና አለስልሱ፤ ግጭትን አውግዙ፤ በግጭት ጎዳናም አትጓዙ። ግጭት የነበረን ታሳጣለች፤ ወደፊት የሚኖርን ትነጥቃለች፤ ከክብር እና ከተድላ ታጎድላለችና።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
