
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ75 ዓመታት ለኢትዮጵያ የእውቀት ብርሃን ያበራ የዕውቀት ቤት ነው ብለውታል።
በትጋት የሚመራ ምርምር፣ በሙግት የሚዳብር ሃልዮት፤ በአመክንዮ የሚበለጽግ ፍልስፍና የዩኒቨርሲቲው መለያ ቀለሞች ናቸው ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ የዕውቀት ብርሃን መፍለቂያ እና የለውጥ ጥሪ ማስተጋቢያ የኾነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ዛሬም የጀመርነውን ልማት በዕውቀት ለመምራት ተደማሪ ጉልበት ነው። ዩኒቨርሲቲው ከምሥረታው ጀምሮ የኢትዮጵያ የለውጥ እና የልማት ጥያቄዎች የፈለቁበት፤ የጊዜው ትንታግ ወጣቶች የለውጥ አብዮት የጎሰሙበት የታሪክም የዕወቅትም ቤት ነው ብለዋል።
ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት የተደረገው ምክክርም ትናንት እና ዛሬን፣ ዛሬን እና ነገን፤ ዘላቂ ብልጽግናን ከተሳካ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ጋር አሠናስሎ ለመምራት ጉልበት የሚሰጥ መኾኑን ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ተምራችሁ፣ በዕውቀት ተኮትኩታችሁና ካባ ጭናችሁ ዛሬ በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ተቋማት ለምታገለግሉ ምሁራንና ባለሞያዎች እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።
የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያ ለመገንባት በርትታችሁ እየተማራችሁ ላላችሁ ጥበብ ፈላጊ ተማሪዎች በሙሉ እንኳን ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት በዓል አደረሳችሁ ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
