
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2025/26 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ብቻ ከ325 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ተቀማጭ በመሰብሰብ አጠቃላይ ተቀማጩን 2 ትርሊዮን ብር አድርሷል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት ተወካይ እና የኮርፖሬት አገልግሎቶች ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ኤፍሬም መኩሪያ ባንኩ ሦስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አጠቃላይ ተቀማጩን በእጥፍ በማሳደግ 2 ትሪሊዮን ብር ማድረሱን ተናግረዋል።
አፈጻጸሙ የ2030 የባንኩ ስትራቴጂ ውጤት መኾኑን ገልጸዋል። ለባንኩ ትልቅ ስኬት መኾኑን አመላክተዋል። ለተገኘው ስኬት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የነበራቸውን ሪጅኖች፣ ዲቪዥኖች፣ ዲስትሪክቶች እና መላውን ሠራተኛችን እና ደንበኞችን አመስግነዋል።
ስኬቱ በቀጣዮቹ ስድስት ወራትም የተሻለ ለመሥራት እንደሚያነሳሳ እና በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 750 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ተቀማጭ ለማሰባሰብ ታልሞ እየተሠራ መመኾኑን ገልጸዋል። ለዚህም ሁሉም የባንኩ ማኔጅመንት እና ሠራተኞች የነበሩ ድክመቶችን በማረምና ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል እንዲሠሩ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቢዝነስ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ደረጀ ፉፋ ባንኩ በ34 ወራት ውስጥ የትሪሊዮን ብስራት መድገሙን አስታውሰዋል። ከባንኩ ሪጅኖች እስከ ቅርንጫፍ ድረስ ለዚህ ስኬት ለመብቃት በርካታ ውጣ ውረዶች መታለፋቸውን ጠቁመዋል።
በበጀት ዓመቱ 6 ወራት ብቻ የተገኘው ተቀማጭ ገንዘብ በየወቅቱ አቅማችንን በእጥፍ እያሳደግን ለመምጣታችን ማሳያ ነው ብለዋል።
ከዚህ የላቀ ስኬት ለማምጣት ሁሉም በጋራ እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
