“ዘላቂ ሰላምን እና ልማትን ለማረጋገጥ ሕዝቡ ፅንፈኞችንና ተላላኪወችን የሚሸከምበት ትክሻ እንደሌለው በሕዝባዊ የውይይት መድረኮች አረጋግጧል ” የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

55

 

ባሕር ዳር: ታሕሣሥ 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክልሉ ሕዝብ ያገኘዉን ሰላም በማፅናት አይቀሬውን የሀገሪቱን የብልፅግና ጉዞ ለማፋጠን እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።

የክልሉ መንግሥት በወቅታዊ ጉዳይ የሰጠው ሙሉ መግለጫ ቀጥሎ ቀርቧል።

የአማራ ሕዝብ በሥርዓተ መንግሥት ምስረታና በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን እህት ወንድም ሕዝቦች ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ አንድነት አወንታዊ ድርሻዉን የተወጣ ህዝብ ነው።

ህዝባችን በርካታ አኩሪ ታሪኮች ያሉት፤ ከክልሉ ባለፈ የሀገራችን ህዝቦች ቋንቋቸው፣ ሃይማኖታቸውና ማንነታቸው ተከብሮ፤ በመቻቻልና በአብሮነት እንዲኖር የሰራ ታላቅ ህዝብ ነው፡፡

ባለፉት ሰባት የለውጥ አመታትም ኢትዮጵያዊ የሆነው ሁሉ ሰባዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ ተከብረውለት በነፃነት እንዲኖር በተካሄደው የለውጥ ጉዞ የክልሉ መንግስት እና ህዝብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳደረጉ የሚታወቅ ሃቅ ነው፡፡ በተለይም በተሳሳተ ትርክት ህዝባችንን ዋጋ ሲያስከፍሉ የቆዩ ግፈኞችን ከሌሎች የሀገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር በጋራ ታግሎ በሃገራችን ታሪካዊ ለውጥ እንዲመጣ የታገለ ህዝብ ነዉ፡፡ በሂደቱም ወጣቶች፣ሴቶች፣የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ፖለቲከኞች እንዲሁም ሌሎች የለውጡ መሪ የነበሩ ሃይሎች ድርሻቸዉ በታሪክ የሚቀመጥ ነው። በሃገራችን የተገኘዉን ለውጥም በለውጥ ፈላጊ ኃይሎች የተባበረ ክንድና በህዝብ ከፍተኛ ድጋፍ ማስቀጠል ተችሏል፡፡

ይሁን እንጂ ለውጡን ለማፅናትና ለማስቀጠል መንገዶቹ ሁሉ አልጋ ባልጋ አልነበሩም። ከለውጡ ጅማሮ አንስቶ የመንግስትን ሆደ ሰፊነት እንደ ፍርሃት በመቁጠር ህዝባችን ያገኘዉን ሁለንተናዊ ድል ለመቀልበስ መልከ ብዙ ፈተናዎችና ጠመዝማዛ መንገዶች ታልፈዋል፡፡ በሴራ ፖለቲካ ተወልደው ያደጉ የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ባዕዳን በመቀናጀት ሀገራችንንና ክልላችንን በጦርነት ለማመስ ያልፈነቀሉት ድንጋይ፣ ያልቆፈሩት ጉድጓድ የለም ብሎ በድፍረት መግለፅ ይቻላል፡፡ በተለይ ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልላችን ፅንፈኛ ቡድኖች የአማራን ህዝብ ትክክለኛ ጥያቄወች እንደሽፋን በመጠቀም ወደ ግጭት በመግባት ህዝብ ላይ ከባድና አሳፋሪ ሰባዊና ቁሳዊ ጉዳት አድርሰዋል፡፡

ይህ ቡድን የህዝብ መጠቀሚያ መሰረተ ልማቶችን አውድሟል፤ የነገ ሃገር ተረካቢ ትዉልድ እንዳይኖር የትምህርት ስርዓቱን አስተጓጉሏል፤ መምህራንን ገድሏል፤ የሚማሩ ህጻናት ላይ ቦምብ በመጣል ጉዳት አድርሷል፤ ከራሱ ሃሳብ ጋር አልሄዱም ያላቸውን ሁሉ በሃሳብ ልዩነት ብቻ ረሽኗል፤ የሃገር ሽማግሌዎችንና የሃይማኖት አባቶችን ገድሏል፤ ሰው የሆነ ፍጡር ያደርገዋል ተብሎ የማይታሰብ ድርጊት በጭካኔ እጅ እና ጆሮ በመቁረጥ የአረመኔነቱን ጥግ በአደባባይ አሳይቷል፣ትርፍ አምራቹ አርሶ አደር ያመረተዉን ለገበያ እንዳይሸጥ እና ግብአት እንዳይቀርብለት ከልክሏል፤የምርትና አገልግሎቶችን እንቅስቃሴ ገድቧል፣ እገታ እና መሰል የሽብር ተግባራትንም በስፋት ፈፅሟል።

ይህ የሽብር ተግባር የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን በተቀናጀ መልኩ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ክልሉን በልዩ ልዩ የሴራ መንገዶች ማዳከም በሚል የሚከተለው እቅድ መሆኑ በግልፅ ሁሉም ሊገነዘበውና ሊታገለው ይገባል፡፡ ይህንን አፍራሽ እቅዱን ለማሳካት ጦር መሣሪያ በማስታጠቅ፣ ወታደራዊ ድጋፍ በመስጠት፣ በፕሮፖጋንዳ በማገዝ፣ በፋይናንስና በሚዲያ በመደገፍ በተቀናጀ መልኩ ታስቦበት የተሠራና የአማራን ህዝብ መሪ አልባ እንዲሆንና አንድነት እንዳይኖረው በማድረግ እርስ በርሱ እንዲባላ የተሸረበ እኩይ ሴራ ነው፡፡

ይሄን እኩይ የፅንፈኞች ድርጊትና ተግባር ለመቀልበስም መንግስት ከታታሪው፣ ከአርቆ አሳቢውና ከሰላም ወዳዱ የክልላችን ህዝብ ጋር በመሆን በወሰደዉ ህግ የማስከበር እርምጃ የፅንፈኞችና የላኪዎቻቸውን ህልም በማክሸፍ ህዝባችን የሰላም አየር መተንፈስ ጀምሯል።

ክልሉን በሁሉንተናዊ መልኩ የማዳከም ፕሮጀክት ያላቸው ባንዳዎችንና ባዕዳንን የፌደራልና የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በቅንጅት አስፈላጊውን ዋጋ ሁሉ በመክፈል ውድ የሆነውን ሰላም በማረጋገጥ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ አንፃራዊ ሰላም እንዲመጣም የጥምር ፀጥታ ኃይላችን አኩሪ ገድል በታሪክ ሲዘከር የሚኖር ነው፡፡

ስለሆነም ከምንም በላይ የተጀመረውን የልማትና የብልፅግና ጉዞ ለማስቀጠልና የአማራን ህዝብ ሁለተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የክልሉ መንግስት ከምንጊዜውም በላይ ርብርብ እንደሚያደረግ፤ አክራሪነትና ፅንፈኝነት ለራሱ ለፅንፈኛውም የማይበጅና የተሸናፊዎች መንገድ በመሆኑ ችግሮችንም በውይይትና በሰላም ለመፍታት የክልሉ መንግስት ምንጊዜም ለሰላም የዘረጋዉ እጁ የማይታጠፍ መሆኑን ይገልፃል፡፡

ታጥቀው ጫካ ሲንንቀሳቀሱ የነበሩ በሽህ የሚቆጠሩ ሃይሎችም የክልሉን መንግስት የሰላም ጥሪ ተቀብለው በመግባት እና ወደ ህብረተሰቡ በመቀላቀል መደበኛ ህይወታቸዉን እንዲመሩ ማድረግ ተችሏል። ይሄ የሰላም ጥሪ አሁንም ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑንም ለማሳወቅ እንወዳለን።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ተጠናክሮ የቀጠለው የፅንፈኞች ተግባር ለአማራ ህዝብ ከፍተኛ በደል እያስከተለ መሆኑንና ታጣቂው ከአማራ ህዝብና ከኢትጵያ ጠላቶች ጋር በመቀናጀት አገር ለማፍረስ በተላላኪነት እያገለገለ መሆኑን የተረዱ ወጣቶችና ቡድኖች መንግስት ያቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ እየተቀበሉ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት መንግስት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ዝግጁነት ውጤት ነው፡፡

መንግስታችን የገጠሙትን ፈተናዎች ሁሉ ተጋፍጦና ተቋቁሞ እንደ ክልል በልማት፣ በሰላምና በልዩ ልዩ ተግባራት በተለየ እምርታዊ ጉዞ ውስጥ ለመግባት ጥረትም አድርጓል፡፡ ተጨባጭ ለውጥም ማስመዝገብ ችሏል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የክልሉ መንግስት የአጭርና የረዥም ጊዜ ስትራቴጅክ ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደስራ በመግባት፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በሳይንስና ቴክኖሎጅ ዘርፎች ዕምርታዊና ተመጋጋቢ ዕድገት በገጠርና በከተማ ለማስመዝገብ ዓልሞ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ በትምህርትና በጤናው ዘርፍም የላቀ ለውጥ ለማምጣት ክፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በግጭት ምክንያት ተስተጓጉለው የነበሩ ትምህርትቤቶችም ተከፍተው ተማሪዎቻቸውን በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡

እየተመዘገቡ ያሉ ተስፋ ሰጭ የልማት ውጤቶችም አሉ፡፡ የከተሞች የኮሪደር ልማት፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በበጋ ስንዴ ልማት፣ የስሚንቶ ፋብሪካዎች— ወ.ዘተ. በቂ ማሳያዎች ናቸው፡፡

ከሥራ አጥነት እና ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዘው ከሕዝባችን የሚነሱ ችግሮችንም ለመፍታት ከመቼውም ጊዜ በላይ በአገልጋይነት መንፈስ ጠንክረን እየሰራን እንገኛለን።

በአጠቃላይ መንግስት የህግ ማስከበሩን ተግባር አጠናክሮ ከማስቀጠል ጎን ለጎን የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ይበልጥ ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ በሰላማዊ ውይይቶች ችግሮችን የመፍታት አማራጭን በመከተል ልማትንና ጥራት ያለው የህዝብ አገልግሎት አሠጣጥ ሥራዎችን ለማስቀጠል በከፍተኛ ትኩረት የሚሠራበት ጉዳይ ይሆናል፡፡

በመሆኑም ዘላቂ ሰላምን እና ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ሕዝቡ ፅንፈኞችንና ተላላኪወችን የሚሸከምበት ትክሻ እንደሌለው በተደረጉት ትልልቅ ህዝባዊ የውይይት መድረኮች ያሳየበትን አቋሙንና የጀመረውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ እናቀርባለን፡፡

አሁንም ድረስ የመንግስትን የሰላም ጥሪ ወደጎን በመተዉ የክልላችንን ሰላም ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ሃይሎችን የማንታገስና የመንግስት ተቀዳሚ ተግባር የሆነዉን ህግ የማስከበር ተግባር አጠናክረን የምንቀጥል መሆኑንም ለማሳወቅ እንወዳለን።
በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም በሀሰተኛ መረጃዎች ሳይደናገሩ በሃገራችንና በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና የማይቀረውን የልማትና የብልጽግና ጉዞ ለማረጋገጥ በምናደርገው ርብርብ የበኩላቸውን አውንታዊ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ
ታህሳስ 2018 ዓ.ም

ባህር ዳር

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ይኽን ትውልድን በአዲስ ብርሃን ነው የምመለከተው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleከደባርቅ-በለስ- መካነ ብርሃን ድረስ የሚገነባው የመንገድ ሥራ ምን ላይ ደረሰ