
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “የባሕር በራችን የደም ስራችን” በሚል መሪ መልዕክት ሀገርአቀፍ የወጣቶች የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ታረቀኝ አብዱልጀበር ንቅናቄው እንደ ሀገር የተጀመረውን የባሕር በር የባለቤትነት ይገባኛል ታሪካዊ እና ጂኦፖለቲካዊ ጥያቄ ድጋፋቸውን ለማሳየት እና የጋራ አቋም ለመያዝ እንደኾነ ጠቁመዋል።
የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አሕመድ ወጣቶች የለውጡ አርበኛ እንዲኾኑ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። የሕልውና ጉዳይ የኾነውን የባሕርበር ጥያቄ የማስመለስ የዚህ ትውልድ ኀላፊነት ነው ብለዋል።
የሀገር ብሔራዊ ጥቅምን በተመለከተ ወጣቶች የጋራ ግንዛቤ ኑሯቸው የጋራ አቋም በመያዝ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ያላትን መብት ለማሳካት መሥራት አለባቸውም ነው ያሉት።
በመድረኩ ወጣቶቹ እንደሀገር ለባሕርበር ጥያቄ ያላቸውን ድጋፍ እና ቁርጠኝነት የአቋም መግለጫ በማውጣት አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን አዘጋጅነት በተካሄደው የንቅናቄ መድረክ ላይ ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ከ1ሺህ በላይ ወጣቶች ተገኝተዋል። የባሕር ኀይል አባላት፣ የወጣት አደረጃጀቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አርበኞች፣ ልዩ ልዩ የጸጥታ አካላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በበዓሉ ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፦ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
