
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የልደት እና የጥምቀት በዓላትን በስኬት ለማክበር ከጸጥታ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
በውይይቱ ሊያጋጥሙ የሚችሉ እንቅፋቶች እና መፍትሔያቸውም ተመላክቷል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው በዓላትን በሰላም ለማሳለፍ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።
ዝግጅቱ ሁሉን አቀፍ ነው ያሉት ኮማንደር ዋለልኝ የትራንስፖርት እጥረት፣ የትራፊክ መጨናነቅ እና አደጋ እንዳይኖር ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የልዩ ተቋማት እና መሠረተ ልማት ፖሊስ የአንደኛ ሻለቃ አዛዥ ኮማንደር ሙሉ መለሰ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ በመወያየት እና አመራር በመቀበል በተገቢው እንሠራለን ብለዋል።
ተቋማትንም በትኩረት እየጠበቅን ነው ያሉት ኮማንደር ሙሉ ሕዝቡም ሰላሙን በባለቤትነት እንዲጠብቅ እና ከጸጥታ ኃይሉ ጋር መተባበር እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።
በዓላቱን ለማክበር እቅድ ተዘጋጅቶ በየደረጃው ውይይት እየተደረገበት መኾኑን ነው የተናገሩት። ማጭበርበር፣ ስርቆት እና ሀሰተኛ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል ከኅብረተሰቡ ጋር በትብብር እንሠራለን ነው ያሉት።
በኬላዎች እና ቁጥጥር በሚያስፈልጋቸው ቦታዎች ሁሉ ትኩረት በመስጠት እንጠብቃለን፤ ለዚህም በየደረጃው የሚገኝ ፖሊስ እና አጋር አካላት በአንድ ዕዝ ሥር ኾነው በተጠንቀቅ ይጠብቃል ብለዋል።
በበዓላት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎችን ችግር እና እንግልት እንዳያጋጥማቸው የመጓጓዣ አገልግሎቶችንም በማመቻቸት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደሚሠራ ተናግረዋል።
በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ ኅብረተሰቡም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ እና ሕዝቡም ደኅንነቱ እንዲጠበቅ ሁሉም የጸጥታ ኃይል በቅድመ ዝግጅት እና በትኩረት እንዲሠራ ይጠበቃል ብለዋል።
መንገዶች እና መንገደኛዎች የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎች፣ የገበያ፣ የበዓላት እና ሌሎች ደኅንነታቸው ሊጠበቁ የሚገባቸው ቦታዎች የጥበቃው አካል መኾናቸውን ጠቅሰዋል።
ሕገ ወጥ ቁሳቁስ፣ ሸቀጦች እና የሀሰተኛ ገንዘብ ዝውውር ቁጥጥር የዝግጅቱ አካል መኾናቸውንም አንስተዋል። ከወጣቶች እና ከሃይማኖት አባቶች ጋር ተመካክሮ እና ተባብሮ በመሥራት ሕዝቡን የሰላሙ ባለቤት ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
ኅብረተሰቡም ለሰላሙ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
