
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፌዴራል እና ከክልል የተውጣጡ ከፍተኛ መሪዎች በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘውን የአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ እና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝን የሥራ እንቅስቃሴ እየተመለከቱ ነው።
በጉብኝቱ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በአማራ ክልል በሚገኙ የአምራቹ ዘርፍ ኢንዱስትሪዎች ላይ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል የገበያ ትስስር አንዱ መኾኑን ተናግረዋል። የአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ እና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ ችግሩ የሚስተዋልበት አንዱ ፋብሪካ መኾኑን ጠቅሰዋል።
የአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ እና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ ራሱን ችሎ ማሽን ማምረት የሚችል እና ለሌሎች ኢንዱስትሪዎች መለዋወጫዎችን ማምረት የሚችልበት የቴክኖሎጅ፣ የሰው ኃይል እና የግብዓት አቅም ያለው ነው ብለዋል። ቀደም ሲል በነበረው የሥራ እንቅስቃሴ ግን በሙሉ አቅሙ እያመረተ አለመኾኑን አንስተዋል። በሙሉ አቅሙ እንዳያመርት ካደረገው ችግር ውስጥ የገበያ ትስስር አንዱ እንደኾነም ነው የገለጹት።
በሀገሪቱ ያሉ የስኳር እና የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በርካታ መለዋወጫዎችን ከሀገር ውጭ ያመጣሉ ያሉት ሚንስትሩ እነዚህ ኢንዱስትሪዎች እዚህ ያለውን አቅም እንዲያውቁ እና እንዲመለከቱ በማድረግ በሁለቱም መካከል የገብያ ትስስር መፍጠር እና ምርታማነትን መጨመር አስፈለጊ መኾኑንም ተናግረዋል።
በጉብኝቱ እየተሳተፋ ያሉ የስኳር ፋብሪካ እና የሲሚንቶ ፋብሪካ ሥራ አሥኪያጆች እንዲህ አይነት አቅም ያለው ፋብሪካ መኖሩን መረጃው እንዳልነበራቸውም ጠቅሰዋል።
ከዚህ ጉብኝት በኋላ ውይይት እንደሚደረግም ይጠበቃል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
