
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል እና የቅዱስ ወንጉሥ ላሊበላ የልደት በዓልን ለማክበር በርካቶች ወደ ላሊበላ ይጓዛሉ፡፡ በተለይም የቤዛ ኲሉ ልዩ ሥነ ሥርዓትን ለመታደም በዚህ ዓመት በርካታ ቱሪስቶች ወደ ላሊበላ እየገቡም ነው፡፡
ከላሊበላ ከተማ አሥተዳደር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው አብዛኞቹ በላሊበላ ሆቴሎችን ጨምሮ የእንግዶችን ቆይታ ያመረ እንዲሆን ያማሩ ዝግጅቶች ተደርገዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም የተጓዦችን ፍሰት ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ወደ ላሊበላ የሚያደርገውን የበረራ ቁጥር ማሳደጉን አሳውቋል።
ከነበሩ መደበኛ በረራዎች በተጨማሪ ከታኅሣሥ 26/2018 ዓ.ም እስከ ጥር 02/2018 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ የበረራ ጭማሪ ማድረጉንም ነው አየር መንገዱ የገለጸው።
ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ለሚመጣው የደንበኞች ፍላጎትም ምላሽ በመስጠት እንደ አስፈላጊነቱ ተጨማሪ በረራዎችን እንደሚያደርግም አሳውቋል።
አየር መንገዱ ተጨማሪ በረራዎችን ከማቅረብ ባሻገር በየከተሞቹ በሚገኙ የትኬት መሸጫ ቢሮዎች ደንበኞች የተመቻቸ አገልግሎት እንዲያገኙ እየሠራሁ ነው ብሏል።
በዓል ወቅት በረራዎች ከመጨመራቸው ጋር ተያይዞ በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ መጨናነቅ እንዳይፈጠር ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝም ለአሚኮ ዲጂታል አሳውቋል።
ዘጋቢ:- ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
