ያለ አግባብ የተመዘበረ ሃብትን በማስመለስ ረገድ በትኩረት መሥራቱን ፍትሕ ቢሮ አስታወቀ።

26
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸሙን ከዞን መምሪያዎች ጋር ገምግሟል።
የቢሮው ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም በክልሉ የ25 ዓመት አሻጋሪ የእድገት እና ዘላቂ ልማት ፍኖተ ካርታ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ሰላም እና ደኅንነትን ማስፈንም የተካተተበት ነው ብለዋል።
የወንጀል ፍትሕ አሥተዳደር ላይ መከላከልን በማስቀደም እንደ ተቋም መሠራቱን እና “የተመዘበረን ሃብት ለማስመለስ በትኩረት መከናወኑን” ገልጸዋል።
ከኤግዝቪት እና ወንጀል ጋር የተያያዘ 595 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ገቢ መደረጉንም በዕለቱ አንስተዋል።
ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት በሙስና ወንጀል የተዘረፈ መሬት መመለሱን እና በወንጀለኞች ላይ ቅጣት መተላለፉን ኀላፊው ጠቅሰዋል።
የመንግሥት እና የሕዝብ ጥቅም ያለባቸውን የፍታብሔር ጉዳዮች በንቃት እና በብቃት በመከራከር እንዲሁም ድርድር በማድረግ 694 ሚሊየን ብር ለመንግሥት ገቢ መደረጉን አንስተዋል።
በወንጀል የተመዘበረ እና ምንጩ ያልታወቀ ሃብት የማስመለስ፣ የሙስና ወንጀሎች ላይ በሁሉም ቦታ የመሥራት፣ ውዝፍ መዝገብን የመቀነስ፣ በሌሉበት የወንጀል ገንዘብ ቅጣትን የማስገባት ሥራ የቀጣይ ትኩረት ከተሰጣቸው መካከል ናቸው ነው ያሉት፡፡
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፍትሕ መምሪያ ኀላፊ አየልኝ ደሳለኝ በዞናቸው የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን እና የንብረት ማስመለስ ሥራ በልዩ ትኩረት መሠራቱን ገልጸዋል። 108 ሚሊየን ብር እና 726 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ መመለሱንም ተናግረዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ፍትሕ መምሪያ ኀላፊ ደመረ ቸሬ በበኩላቸው በዞናቸው የመንግሥት እና የሕዝብን ጥቅም የሚጎዱ ጉዳዮች ላይ እና የትራንስፎርሜሽን እቅዱ በትኩረት መሠራቱንም አንስተዋል።
ምንጩ ያልታወቀ 125 ሚሊየን ብርም መመለሱን ገልጸዋል። በመደበኛ እና በኢኮኖሚ ወንጀል ደግሞ 164 ሚሊየን ብር ገቢ መደረጉን አንስተዋል፡፡
በውይይቱ የቀጣይ ወራት የትኩረት መስኮች እና አቅጣጫዎች ወይይት ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሕዝባችንን ለችግር የዳረገውን የጸጥታ ችግር በሰላም ለመፍታት መንግሥት እየሠራ ነው።
Next articleየጤና መድኅን አገልግሎትን ማስፋት ሕይዎትን መታደግ ነው።