የአገው ፈረስ ባሕልን በዩኒስኮ ለማስመዝገብ አስፈላጊ ሥራዎች ተጠናቅቀዋል።

41
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአገው ፈረሰ ባሕልን በዩኔስኮ የሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት ለማስመዝገብ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር እና የጥናት ወርክሾፕ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) የአገው ሕዝብ ለዓመታት ሲጠይቀው የነበረው አንጋፋው የአገው ፈረስ ባሕልን በዩኒስኮ የማስመዝገብ ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ አስፈላጊ ሥራዎች ተጠናቅቀዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባለብዙ ሃብት ባለቤት በመኾኗ እነዚህን የሀገር ፀጋዎች ለዓለም በማስተዋወቅ የቱሪዝም ሃብት እንዲኾኑ ትኩረት ተሠጥቶ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
በክልሉ በቅርቡ የጣና ሐይቅ ደሴት ገዳማትና አዋሳኝ ባሕረ ሸሽ መልክዓ ምድር ዓለም አቀፍ ቅርስ ሆነው እንዲመዘገቡ እየተሠራ ያለውን የቅድመ ዝግጅት ሥራም ለአብነት አንስተዋል።
በቀጣይም ክልሉን በብዙ ዘርፍ ወደ ተሻለ ለውጥ ለማምጣት እየተሠራ ነው ብለዋል። የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው እንዳሉት የአገው ፈረስ ባሕል ከሀገር ክብርና ፍቅር ጋር የተሳሰረ የበርካታ እሴቶች ባለቤት ነው።
“በአብሮነት መንፈስ ዘመናትን የተሻገረው የአገው ፈረስ ባሕል የትላንት ታሪካችን፣ የዛሬ ጥንካሬያችን እና የነገ ሕብረ ብሄራዊነት አንድነታችንን የምንገልጽበት የአርበኝነት ቅርሳችን ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
ከአድዋ ድል ማግስት የተመሠረተው የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ከ62 ሺህ በላይ አባላትን አቅፎ በኅብረ ብሔራዊነት ኃይል ጎልቶ የቆመ የኅዝብ ተቋም መሆኑንም ተናግረዋል።
የአገው ፈረስ ባሕልን በዩኒስኮ ለማስመዝገብ እርብርብ ሲያደርጉ ለቆዩ አጋር አካላትንና ተቋማትም ምስጋና አቅርበዋል።
የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ.ር) የአገው ፈረስ ባሕል በዩኔስኮ መመዝገቡ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶችን ቁጥር እንደሚጨምር፤ የሀገሪቱን ኢኮኖሚም እንደሚያነቃቃ ነው የገለጹት።
ከዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ፈንድ እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ለጋሾች ድጋፍ ለማግኘትም ዕድል ይፈጥራል ብለዋል። የማኅበረሰቡን ተሳትፎ እና ማኅበራዊ መስተጋብር የበለጠ እንደሚያጎለብትም አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ሰመሀል ፍስሀ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleፋይዳ መታወቂያ ለሴቶች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ያስገኛል።
Next articleበቡሬ ዙሪያ ወረዳ በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀበሉ።