ፋይዳ መታወቂያ ለሴቶች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ያስገኛል።

26
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የፋይዳ መታወቂያ አካታችነትን ለማጎልበት የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ ከተለያዩ ተቋማት ከተውጣጡ ሴት አደረጃጀቶች እና መምሪያ ኀላፊዎች ጋር በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ሴቶች ለሴቶች ክብር እና ዕውቅና ለመስጠት፣ ከማይታዩበት ሁኔታ ወደ ሚታዩበት እና የሚቆጠሩበት አቅጣጫ የሚመራ፣ ለመንግሥት እና ለግል አገልግሎቶች በቀላሉ ለማድረስ ያግዛል ብለዋል።
ማንነታቸውን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማረጋገጥ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያግዝ መሠረታዊ መሳሪያ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ኀላፊዋ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ሴቶችን ከባንክ አገልግሎት፣ ከማኅበራዊ ድጋፍ ፕሮግራም፣ ከጤና እና ከትምህርት አገልግሎቶች ጋር በቀጥታ እንዲገናኙ የሚያስችል መኾኑን በመጠቆም የሴቶች መብት ጥበቃን እና የማኅበራዊ ፍትሕን ለማስፋትም አስፈላጊ እንደኾነ አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይም 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሴቶችን እና 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን የሚኾኑ ሕጻናትን እስከ የካቲት 30/2018 ዓ.ም ድረስ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ ሁሉም በየአደረጃጀቱ የበኩሉን ርብርብ ሊያደርግ ይገባልም ብለዋል፡፡
የማዕከላዊ ጎንደር ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ቀኑ ቢያድጎ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ለሴቶች እና ሕጻናት ያለውን ጥቅም ለማኅበረሰቡ በማስረዳት ተጠቃሚ እንዲኾኑ የተቀናጀ ሥራ እየሠሩ መኾኑን አመላክተዋል።
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የፖለቲካ ጉዳይ ሳይኾን ሴቶች እና ሕጻናት ማግኘት የሚገባቸውን አገልግሎቶች በነጻ ማግኘት እንዲችሉ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በቀጣይ ሁሉም ሴቶች የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ እንዲኾኑ መሥራት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
የአማራ ክልል ሴቶች ማኅበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር እንየ ገነቱ ደግሞ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ሴቶች የትኛውንም አገልግሎት በቀላሉ እና ያለውጣ ውረድ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል ነው ያሉት፡፡
በውይይቱ ወቅት የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ለማውጣት ያጋጠሙ ችግሮች ተነስተው ውይይት ተደርጓባቸዋል።
ተግዳሮቶችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም ተጠቅሷል።
ዘጋቢ፡- ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሴት ተማሪዎችን ተሳትፎ በማጎልበት በአመለካከት እና በክህሎት ብቁ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው።
Next articleየአገው ፈረስ ባሕልን በዩኒስኮ ለማስመዝገብ አስፈላጊ ሥራዎች ተጠናቅቀዋል።