ባሕላዊ የእርቅ ሥርዓቶች ማኅበራዊ መስተጋብሮችን ሲያሳልጡ የኖሩ እሴቶች ናቸው።

4
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የባሕል ፍርድ ቤቶች እውቅና መስጫ እና የሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብርን አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ የፌዴራል እና የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ከየወረዳው የተወከሉ ሽማግሌዎች፣ እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
እውቅና ተሰጥቷቸው ሥራ የጀመሩት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች 15 አይነት ሲኾኑ እነሱም ሽምግልና፣ አበጋር፣ ⁠ረከቦት፣ ዱለት፣ ⁠አማሬ ቁና፣ አውሳይድ፣ ⁠ጎራው አባ አሊ፣ ⁠ስምንቱ ማይ ቤት፣ ⁠ዘወልድ፣ መዛርድ፣ ክፍሎ፣ ሰንዬሰገድ፣ አባ ሀጋ፣ ዙፋን ዋልዋጅ፣ እና ሰባቱ ከዘራ ናቸው።
በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) አማራ ክልል የበርካታ እሴቶች ባለቤት ነው ብለዋል።
የክልሉ ሕዝብ አለመግባባቶችን የሚፈታባቸው እና እርቅን የሚያሰፍንባቸው የዳበሩ ባሕላዊ ሥርዓቶችም እንዳሉት ጠቁመዋል። እነዚህ ሥርዓቶች ከመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት ጎን ለጎን ፍትሕ እና ርትዕን የሚያስገኙ፤ ሴቶች፣ ሕጻናት እና አቅመ ደካሞችም በደል በደረሰባቸው ጊዜም ማኅበራዊ ፍትሕን የሚሰጡ ናቸው ብለዋል።
የባሕል ፍርድ ቤቶች ዕውቅና አግኝተው እና በሕግ ተደራጅተው ወደ ሥራ መግባታቸው ጥቃትን የማይታገስ እና ለፍትሕ እና ርትዕ የቆመ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት።
አማራጭ የፍትሕ ሥርዓት በመዘርጋትም ሕዝብን የሥርዓቱ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ነው ያሉት። የአካባቢን ጉዳይ በዚያው አካባቢ ባሕላዊ ሥርዓቶች በማስታረቅ ሰላም እና ደኅንነትን የሚያረጋግጥ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
በክልሉ እውቅና አግኝተው ሥራ የጀመሩት ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች በተለይም ጎጅ ልማዶች እንዲቀሩ ከማድረግ እኳያ ጠንክረው እንዲሠሩም መልዕክት አስተላልፈዋል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸውም ፍርድ ቤቶቹ ለሚያከናውኑት ሥራ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታው ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ.ር) የግጭት መፍቻ ባሕሎች ለዘመናት ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩ እሴቶች መኾናቸውን አንስተዋል። የሰዎችን ማኅበራዊ መስተጋብሮች ሲያሳልጡ የኖሩ እሴትች ስለመኾናቸውም ገልጸዋል።
እንደ ሀገር እነዚህን ባሕላዊ የእርቅ ሥርዓቶች ደግፎ እና የሕግ ማዕቀፍ አበጅቶ ሥራ ላይ የማዋል ሥራ አለመከናወኑንም አስታውሰዋል። የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያውን ተከትሎ ግን ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች እውቅና ተሰጥቷቸው እንዲሠሩ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓትም አማራ ክልልን ጨምሮ ሰባት ክልሎች ሕግ አውጥተው ባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን እየተጠቀሙ ይገኛሉ ብለዋል። አማራ ክልል ከገጠመው ወቅታዊ የግጭት ሁኔታ በአጭር ጊዜ በመውጣት ይህንን የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀቱ ልዩ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል።
ፍትሕ ሚኒስቴር በሁሉም ክልሎች ባካሄደው ጥናት መሠረት ከ80 በመቶ በላይ ሰዎች በባሕል ፍርድ ቤት የመዳኘት ፍላጎት እንዳላቸው ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።
በግጦሽ መሬት፣ በውርስ፣ በፍች፣ እና በመሳሰሉት መንገዶች ከሚከሰቱ አለመግባባቶች ውስጥ 43 በመቶው መፍትሔ የሚያገኙት በባሕላዊ እርቅ ስለመኾኑም ዶክተር ኤርሚያስ ተናግረዋል። ይህም የሚያሳየው የሕዝቡ በባሕላዊ ፍርድ ቤቶች የመዳኘት ፍላጎት ከፍተኛ መኾኑን የሚያሳይ ስለመኾኑ አስረድተዋል።
ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች በአማራ ክልል እውቅና ተሰጥቷቸው ሥራ እንዲጀምሩ መደረጉ በወቅቱ የሚታዩ ግጭቶች እንዲፈቱ የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አመላክቸዋል።
መሥሪያ ቤቱ ባሕላዊ የግጭት መፍቻ መንገዶች እንዲስፋፉ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው ወደፊትም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሕዝብን ለመካስ እና ለማገልገል የሰላም አማራጭን ተቀብለናል።
Next articleወንጀለኞችን ማጋለጥ ለጋራ ሰላም መፍትሔ ነው።